የሐዘን መግለጫ ከኢትዮጵያ ስፖርት ፌደሬሽን በሰሜን አሜሪካ (ESFNA)

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ በመጀመርያው የፌዴሬሽኑ ፕሬዚደንት በአቶ ፍስሃ ወልደአማኑኤል ዜና ዕረፍት የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እንገልፃለን::

⚽ ለፌዴሬሽኑ የነበራቸው አስተዋጽኦ

* የመጀመሪያው ፕሬዚደንት፦

ፌዴሬሽናችን የድርጅት ቅርፁን በያዘበት በ1985 ጋሽ ፍስሃ የመጀመሪያው የፌዴሬሽኑ ፕሬዚደንት ሆኖ ተመርጦ ነበር::

* የ፵፪ ዓመታት ታማኝነት፦

ከ1985 ጀምሮ ለቀጠሉት ለ42 አመታት ያለማቋረጥ በፌዴሬሽኑ አመታዊ በዓል ላይ ተገኝቷል:: በ2026 በዓላችን ላይ በህመም ምክንያት ሊገኝ ባለመቻሉ አለመኖሩ አጉድሎ ነበር::

* የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፦

የፕሬዚደንትነቱን ሃላፊነት ሲጨርስ በፌዴሬሽኑ የእግር ኳስ ውድድር ክፍል ውስጥ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ከ35 አመታት በላይ በበጎ ፈቃደኝነት አገልግሏል።

“በጎ ስራ የህይወት ስንቅ ነው” — ጋሽ ፍስሃ ይህንን ሲል አድርጎትና ኖሮት ስለሆነ ከትክክለኛው ሰው የወጣ ትክክለኛ ቁምነገር እንደሆነ የፌዴሬሽኑ ቤተሠብ በሙሉ ይረዳዋል::

የህይወት ታሪክ እና በእግር ኳስ ሜዳ ላይ የነበራቸው ገድል

* ትውልድና እድገት፦

ጋሽ ፍስሃ ወልደአማኑኤል ከሐረር ከተማ ወጣ ከምትል ደደር ከምትባል ትንሽ ቀበሌ ነው የተወለደው:: እስከ ስድስት አመቱ ያደገና የተማረው ሐረር ሲሆን ከልጅነቱ ጀምሮ በኳስ ፍቅር ተከትቧል::

* የቅዱስ ጊዮርጊስና የብሔራዊ ቡድን ዘመን፦

ቤተሰቡ ወደ አዲስ አበባ ሲዛወር በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት እየተማረ ነበር በቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን ተመልምሎ መጫወት የጀመረው:: ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የአዲስ አበባ እና የኢትዮጵያ ሻምፕዮናን ደጋግሞ አሸንፏል:: በብሄራዊ ቡድን ደግሞ ከ4ኛ እስከ 7ኛ የአፍሪካ ዋንጫ አገሩን ወክሎ ተጫውቷል።
(አንዳንዶቹን ከአሜሪካን አገር እየተመለሰ ነበር የተጫወታቸው)::

* የቅጽል ስሞቻቸው፦

ጋሽ ፍስሃ በከረረ የሩቅ ምቶቹ ስለሚታወቅ “መድፈኛው”፤ እጅግ ጥበበኛ ተጫዋች ስለነበረ ደግሞ “ኳስ ፊደሉ” የሚሉ ቅጽል ስሞች ነበሩት::

* የትምህርትና አሜሪካ ህይወት (UCLA)፦

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1969 በእግር ኳስ ስኮላርሺፕ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ ሎስ አንጀለስ (UCLA) መጣ:: በዚያ ቡድን ውስጥ ከኢትዮጵያ ጀምሮ አብረውት የተማሩና የተጫወቱ እነ ሸዋንግዛ አጎናፍር፣ ተቀዳ አለሙ፣ ሰለሞን ተርፋ እና ሌሎችም ድንቅና ታዋቂ ተጫዋቾች ነበሩ::

* የአለም አቀፍ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ዘመን፦

በዩኒቨርሲቲ የጀመረውን ብቃት በፕሮፌሽናልነት ቀጥሎበት የ Major League Soccer (MLS) ቀዳሚ በነበረውና እነ ፔሌ በሚጫወቱበት ሊግ ውስጥ ለሎስ አንጀለስ አዝቴካ ቡድን ከታዋቂው እንግሊዛዊ ጆርጅ ቤስት ጋር በአንድ ቡድን ተጫውቷል:: እንደ ባላጋራ ደግሞ ከእነ ፔሌ፣ የጀርመኑ ሄንዝ ቤክንባወር እና ጌርድ ሙለር፣ የፖርቱጋሉ ኢዞቢዮ፣ የኔዘርላንዱ ዦአን ክሩይፍ ጋር ተጫውቷል::

የትምህርት ደረጃ እና የበጎ አድራጎት ስራዎች

* የትምህርት ዝግጅት፦

ጋሽ ፍስሃ ከእግር ኳሱ ጎን ትምህርቱን ቀጥሎ ከ UCLA በባችለር፣ ከሁለት ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ የተለያዩ ሁለት የማስተርስ ዲግሪዎችን አግኝቷል::

* የማህበረሰብ አገልግሎት፦

በ1978 በሎስ አንጀለስ ከተማ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር የመጀመሪያውን የሎስ አንጀለስ ስታርስ ቡድንን ከመሰረቱት አንዱ ነበር::

* “አጋር” የበጎ አድራጎት ድርጅት፦

ባለፉት 27 አመታት “አጋር” የሚባል ኢትዮጵያ ውስጥ ረዳት የሌላቸውን ተማሪዎች የሚረዳ የረድኤት ድርጅት አቋቁሞ ብዙ ተማሪዎችን እስከ ዶክተርና ሌሎች ፕሮፌሽናል ዲግሪዎች ድረስ አስተምሯል::

ማህበራዊና ቤተሰባዊ ህይወት

ጋሽ ፍስሃ በሚኖርበት በሎስ አንጀለስ፣ ካሊፎርኒያ በማህበረሰቡ የተከበረ፣ ከሁሉም ሰው ጋር መግባባት የሚችል፣ አገሩንና ህዝቡን የሚወድ፣ በጋብቻ ከ50 አመታት በላይ የኖረ የሁለት ሴት ልጆች አባት እና የአራት የልጅ ልጆች አያት ነበር::

በፌዴሬሽናችን ስም ለባለቤቱ ለወይዘሮ አልማዝ፣ ለልጆቹ ለፅዮን እና ናኦሚ እንዲሁም ለመላው ቤተሰቡ፣ ወዳጅና ዘመዶቹ መፅናናትን እንመኛለን::

የፌዴሬሽናችን አመታዊ ዝግጅት ላይ ግርማ ሞገሳችን መሆንህ በመንፈስ ይቀጥላል:: ፈጣሪ ነፍስህን በእቅፉ ያኑርልን!

“በጎ ስራ የሕይወት ስንቅ ነው!” (የጋሽ ፍስሃ ወልደአማኑኤል የኑሮ መሪ ቃል)

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2