አዲስ አበባ ዉስጥ በተያዘዉ አገራዊ ምክር ላይ የሚሳተፉ 3 የፖለቲካ ፓርቲዎች በምክር ሒደቱ ቅሬታ፣ ጥርጣሬና ሥጋት እንደተሰማቸዉ አስታወቁ። እናት ፓርቲ (እፓ) ፣የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በየፊናቸዉ ባወጧቸዉ መግለጫዎችና ደብዳቤ እንዳሉት ምክክሩ እንዲሳካ ሒደቱ ሊታረም ይገባል።እናት ፓርቲና የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ቅሬታና ማሳሰቢያቸዉን በየፊናቸዉ ባወጡት መግለጫ ሲያስታዉቁ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በምክክር ሒደቱ ላይ ያለዉን ቅሬታ ለምክክር ኮሚሽን ለሶስተኛ ጊዜ በፃፈዉ ደብዳቤ መግለፁን አስታዉቋል።
እናት ፓርቲ በመግለጫዉ የምንመካከረው “አዲስ የእርስ በእርስ ጦርነት ለማዋለድ አይደለም” ሲል ሂደቱ ላይ ከፍተኛ ሥጋት እንዳለው ገልጿል።በምክር ሒደቱ የአዲስ አበባ ከተማን ለአንድ ቡድን ለማስረከብ እና “አዲስ የፀብ ግንባር ለመቀስቀስ” ጥረት እንዳለ መታዘባቸውን የፓርቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሠይፈ ሥላሴ አያሌው ገልፀዋል።ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ባወጣዉ መግለጫ ደግሞ ሐገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ «ሁሉም የበኩሉን ያበርክት” የሚል ጥሪ አድርጓል።የፓርቲው መግለጫ አክሎም “የምክክር ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ የአንድ ወገንን ፍላጎትን በሌሎች ላይ ለመጫን ከሚደረግ ሙከራ መራቅ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በምክክር ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ከሚያደርጉ አፍራሽ ተግባራት መቆጠብ ያስፈልጋል።” በማለት አሳስቧል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ተስተዋሉ ያላቸው ችግሮች ካልተስተካከሉ ከሂደቱ መውጣትን ጨምሮ «ተገቢ የፖለቲካ አቋም» ያለዉን እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።አብን እንደሚለዉ በአዲስ አበባ ዙሪያ “አንድ ወገን በተደራጀ የቁጥር ብልጫ ሌላውን በሚደፈጥጥበት የድምፅ ውድድር ሊስተናገድ አይገባም” ሲል “የአዲስ አበባን አጀንዳ ከዚህ በላይ ለማስኬድ መሞከሩ ሀገራችንን ካለችበት ችግር የባሰ ውጥረት ውስጥ የሚከት በመሆኑ በአስቸኳይ ንግግሩ እንዲቆምና አጀንዳው እንዲያርፍ” አሳስቧል።ከ4ሺሕ በላይ ሰዎች ተሳትፈዉበታል የተባለዉ አገራዊ ምክክር በይፋ ከተጀመረ ነገ ወር ይደፍናል።
የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ሰለሞን ሙጬ እንደዘገበዉ 29 ቀናት ያስቆጠረው ጉባኤ ለጥቂት ዓመታት ረገብ ብሎ የቆየውን የአዲስ አበባ ከተማን ጉዳይ ዳግም አንስቶ ተጨማሪ ውዝግብ እንዲቀሰቀስ ምክንያት መሆኑ ተስተውሏል።
DW Amharic

Source: Yeneta Tube








No comments yet.