ኢትዮጵያዊ የዓይን ሐኪም ዶክተር ጳውሎስ ቀነዓ የሽኝት ሥነ-ሥርዓት ተከናወነ

- Advertisement -
Sidebar AD


‎#Ethiopia | ​የኢትዮጵያ የዓይን ሕክምና ታሪክ ሕያው ተምሳሌትና የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የዓይን ሐኪም የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ጳውሎስ ቀነዓ ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸውን ተከትሎ፣ ታላላቅ የአገር ባለውለታዎችና የሕክምናው ማኅበረሰብ በተገኙበት ሽኝት ተደረገላቸው።

‎ላለፉት 62 ዓመታት ሙሉ ሕይወታቸውን ለዜጎች ዕይታ መታደግና ለዘርፉ ዕድገት የሰጡት እኚህ ታላቅ ሰው፣ በ93 ዓመታቸው ነሐሴ 2 ቀን 2018 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ተከትሎ የመጨረሻ የሽኝት መርሃ ግብራቸው በኢትዮጵያ ወንጌላዊያን ሉተራን ቤተክርስቲያን ተከናውኗል።

‎​ዶክተር ጳውሎስ ቀነዓ በ1956 ዓ.ም. ከቤሩት አሜሪካዊ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ አገራቸው ሲመለሱ፣ የኢትዮጵያ የዓይን ሕክምና ሙሉ በሙሉ በውጭ አገር ዜጎች ላይ የተመሰረተ ነበር። እርሳቸው ግን ከውጭ አገር የሥራ ዕድሎች ይልቅ ሕዝባቸውን ማገልገልን መርጠው በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ሥራቸውን የጀመሩ ሲሆን፣ ለአንድ ሚሊዮን ሕዝብ አንድ የዓይን ሐኪም ብቻ በነበረበት በዚያ ፈታኝ ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በየቀኑ በታማኝነትና በብቃት አገልግለዋል።

‎ከሕክምናው ባሻገር፣ አገሪቱ ያለባትን የከፋ የባለሙያ እጥረት ለመቅረፍ በ1972 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር የመጀመሪያውን የዓይን ሕክምና የድህረ-ምረቃ ፕሮግራም በመመሥረትና “የኢትዮጵያ የዓይን ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበርን” በመፍጠር ረገድ ቀዳሚውን ሚና ተጫውተዋል።

‎​ለዓይን ጤና ባላቸው ልዩ ፍቅር የተነሳ ብቸኛ ሴት ልጃቸውን “ብሌን” ብለው የሰየሙት ዶክተር ጳውሎስ፣ በሀብታምና በደሃ፣ በባለሥልጣንናፐ በምስኪን መካከል ልዩነት ሳያደርጉ የኖሩ የሙያ ሥነ-ምግባር አርአያ ነበሩ።

‎በሕይወት ዘመናቸውም ከዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የጤና ክብካቤ ማኅበር የሕይወት ዘመን ብቃት ሽልማትን ጨምሮ በርካታ ዕውቅናዎችን አግኝተዋል።

‎ላለፉት 62 አመታት በሙያቸው ያገለገሉት ዶክተር ጳውሎስ ቀንኣ የአንዲት ሴት ልጅ አባትና የአንድ ልጅ አያት የነበሩ ሲሆን
‎የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም ዊንጌት አካባቢ በሚገኘው በጴጥሮስ ወ ጳውሎስ ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል።

‎#DrPaulosKenea ​#EthiopianOphthalmology
​#EthiopianMedicalHistory #RestInPeaceDrPaulos
​#LightOfEthiopia ​#MedicalPioneer ​#Ethiopia









Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2