ፊልመኞቹ፥ በአሜሪካ የቀሩ አትሌቶች አስገራሚ ድራማ

- Advertisement -
Sidebar AD

‼️

ከአንድ ቀን በፊት ማክሰኞ ነሀሴ 5/2018፥ በአሜሪካ ፖርትላንድ ኤርፖርት ውስጥ የኢትዮጵያን መለያ የለበሱና ከ20 አመት በታች የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳተፉ የኢትዮጵያ ልዑካን ያሳዩት ድራማዊ ትዕይንትና ትርምስ አስገራሚ ነበር፤ የአሰልጣኞችና የአትሌቶች ልዩ ትወና፥ የአመራሩ ሩጫና ግርግር ሙሉ ፊልም የሚወጣው ክስተት ሆኖ አልፏል፤ ሀትሪክ ስፖርት ኦፊሻል ሰባት የቡድኑ አባላት የመኮብለላቸውን ዜና ይፋ ካደረገ በኋላ ጉዳዩ እስካሁን መነጋገሪያ ሆኖ ቀጥሏል፤ ይህንን ዜና ተከትለን እኛም ጥልቅ ማጣራት አድርገን ተጨማሪ ዝርዝር መረጃዎችን ይዘን ቀርበናል፥ እነሆ የፊልመኞቹ ድራማ፦

🔷 የአሰልጣኞቹ መሰወር፦
አራት አሰልጣኞች ወደ አሜሪካ ሄዱ፤ ኢንስትራክተር መሰረት መንግስቱ፣ ሀብታሙ ግርማ፣ ድሪባ ለገሰና አማረ ሙጬ

ከቡድኑ ጋር አብሮ የተመለሰው ግን ኢንስትራክተር መሰረት መንግስቱ ብቻ ነው፤ ሁለቱ አሰልጣኞች ሀብታሙ ግርማና ድሪባ ለገሰ ፖርትላንድ ኤርፖርት ድረስ ከቡድኑ ጋር አብረው በአንድ መኪና ተጉዘው ነበር፤ ሀብታሙ ዘመድ ጋር ለአንድ ሳምንት መቆየት እፈልጋለሁ ብሎ ትኬቱን አራዝሟል፤ በአንድ ኤርፖርት ስለምንሳፈር አብሬ ልሂድ ብሎ የቡድኑ የመኪና ጉዞ አንዱ አካል ሆነ፤ አሰልጣኝ ድሪባ ግን ወደ አዲስ አበባ ተመላሽ ነበር፤ ልዑኩ ወደ ውስጥ ሲገባ ሁለቱ አሰልጣኞች ማንንም ሳይሰናበቱ ተሰወሩ፤ የመጀመሪያ ፈር ቀዳጆች እነሱ ሆኑና ቡድኑ ውስጥ ድንጋጤ ተፈጠረ

አሰልጣኝ ሀብታሙ እንደሚመለስ ለፌዴሬሽኑ ማሳወቁ ተሰምቷል፤ ሆኖም ለውድድሩ የሄደበት መንገድ በስራ አስፈፃሚው ዘንድ ግርታን ፈጥሯል፤ የሁሉም ተሳታፊ ልዑካን ትኬትና ሌሎች አቅርቦቶች ስራ አስፈፃሚው አምኖባቸው በፅህፈት ቤቱ ሃላፊ ዶ/ር አመንሲሳ ከበደ በኩል የተፈፀሙ ናቸው፤ የሀብታሙ ግን በፕሬዝዳንቱ ኮማንደር ስለሺ ስህን ግላዊ ውሳኔ የተከናወነ በመሆኑ ስራ አስፈፃሚዎቹ ጥያቄ ማንሳት ጀምረዋል፤ እኛ መሄዱን አናውቅም፥ አልወሰንም እያሉ ነው፤ የሀብታሙ መመለስ አልያም አለመመለስ ግን ከአንድ ሳምንት በኋላ ይታወቃል

ወደ አዲስ አበባ ተመላሽ የነበረውና ከፖርትላንድ ኤርፖርት ደጃፍ የተሰወረው አሰልጣኝ ድሪባ ለገሰ በክለቡ ኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ከአራት ወራት በላይ ደሞዝ ያልተከፈለውና በተለያዩ አሰራሮች ቅሬታ ያለው በመሆኑ ከማይመለሱት ውስጥ እንደሆነ ተሰምቷል፤ ሁለቱን አሰልጣኞች ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም

ሶስተኛው አሰልጣኝ አማረ ሙጬ ኤርፖርት ድረስ አልሄደም፤ ቀደም ብሎ ቤተሰብ ጥየቃ በሚል ከቡድኑ ማረፊያ ተለይቶ ወጥቷል፤ አሰልጣኙን በስልክ አግኝተን አነጋግረነዋል፤ በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ሃገር ቤት እንደሚመለስ ይህንንም ለፌዴሬሽኑና ለክለቡ ማሳወቁን ነግሮናል፤ የአትሌቶቹን አስገራሚ ድራማ ደግሞ እንቀጥል፦

🔷 መፀዳጃ ቤት ገብቶ ያልተመለሰው፦
ነጋሄ እያሱ የአዳማ አትሌቲክስ ክለብ አትሌት ነው፤ በውድድሩ በ800 ሜትር ተሳትፏል፤ በመጀመሪያው ዙር አንደኛ ቢወጣም በግማሽ ፍፃሜው ሰባተኛ ሆኖ አጠናቆ ለፍፃሜው ሳይደርስ ቀርቷል፤ በጉዞው እለት ፖርትላንድ ኤርፖርት ውስጥ ገንጠል ብሎ ወደ ሌላ አቅጣጫ ሲሄድ አንድ አመራር ያየውና ወዴት ነው ይለዋል፤ መፀዳጃ ቤት ነኝ ብሎ ሻንጣውን አስቀምጦ ገባ፤ አልተመለሰም፤ በሌላ በር ወጥቶ ሄደ፤ አትሌቱ እንደኮበለለ የተረዱት አመራሮች ሌሎቹ ላይ ትኩረት ማድረግ ጀመሩ፤ አስገራሚው ነገር አትሌት ነጋሄ ኤርፖርት ድረስ እየገፋ ይዞት የመጣው ሻንጣ ባዶ ነበር፤ ባዶውን ሻንጣ ትቶላቸው ሄዷል፤ ፊልም መሳይ ክስተት

🔷 ፈጣኗ የኤርፖርት አትሌት፦
እመቤት ጥላሁን በ5ሺህ ሜትር ተሳትፋ ስድስተኛ ሆና ያጠናቀቀች አትሌት ነች፤ የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን አትሌቷ ባለ ባዶ ሻንጣውን ነጋሄን ተከትላ ከኤርፖርት ከጠፉት አትሌቶች ሁለተኛዋ ሆናለች፤ እሷ ግን ሻንጣዋን ይዛ ነው የወጣችው፤ አመራሮቹ ቀድሞ የጠፋውን አትሌት ለመፈለግ ሲበታተኑና ለኤርፖርት ፖሊስ በማሳወቅ ላይ እያሉ ፈጣኗ የኤርፖት አትሌት እልም ብላ ተሰውራለች፤ ሁለቱም አትሌቶች ውጪ የሚጠብቃቸው ቤተሰብ ስለነበር ሊገኙ አልቻሉም

🔷 ትኬት ያሰረዘችው አትሌት፦
ፃድቃን መኮንን በውድድሩ ግፍ ከተሰራባቸው አትሌቶች አንዷ ነች፤ በ3ሺህ መሰናክል ትሮጫለሽ ተብላ ብትመጣም ሳትሳተፍ ቀረች፤ ባለመሮጤ ደብሮኛል፤ ሜዳሊያ በማግኘታችን ግን ደስ ብሎኛል ብላ ለልዩ ስፖርት አስተያየቷን ሰጥታ ነበር፤ በዚህ ክረምት ከጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ተመርቃ ኢትዮ ኤሌክትሪክን የተቀላቀለችው ወጣቷ ፃድቃን በስሟ ባጅ ስላልተዘጋጀላት በሌላ ሰው በወንድ ስምና ፎቶ ባጅ ነበር ስታዲየም ስትገባ የቆየችው፤ አትሌቷ ቺካጎ ዘመድ ስላለኝ ቆይቼ ልምጣ ብላ ጥያቄ ብታቀርብም ፌዴሬሽኑ ከለከላት፤ ትኬቷን ለዘመዶቿ ልካ ከቺካጎ ወደ አዲስ አበባ በራራዋን አሰረዘች፤ ከፖርትላንድ እስከ ቺካጎ ከቡድኑ ጋር ሄዳ ቺካጎ ቤተሰቦቿ ጋር ለመቆየት ወሰነች፤ ይህንን ለማንም አልተናገረችም፤ ፖርትላንድ ኤርፖርት ትኬቷ ሲታይ ግን ሙሉ በሙሉ ተሰርዟል፤ ስትጠየቅ ያሰረዝኩት ከቺካጎ አዲስ አበባ ያለውን ብቻ ነው አለች፤ እዛው ትኬት ቢፈለግ ጠፋ፤ ከሸኚዎቹ መካከል ለነበሩ የአትሌቶች ማናጀሮች በአደራ ተሰጥታ ፖርትላንድ ቀረች፤ መመልስ አለመመለሷ ገና አለየም

🔷 በእርምጃ ተሳትፎ በእርምጃ የቀረው፦
ነገሮ አዱኛ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አትሌት ነው፤ በሻምፒዮናው በ5ሺህ ሜትር እርምጃ ተወዳድሮ 19ኛ ሆኖ አጠናቋል፤ የመጨረሻው ኮብላይ እሱ ሆኗል፤ የቡድን መሪዋ አትሌት መሰረት ደፋርና የቴክኒክ መሪው ኮማንደር ቶሌራ ዲንቃ እንዲሁም ሸኚ የነበሩት ማናጀሮችና የአትሌቲክሱ ወዳጆች ቀደም ብለው የጠፉትን ፈልገው ካጧቸው በኋላና ለኤርፖርቱ የፀጥታ ሀይሎች ካሳወቁ በኋላ ከፖርትላንድ ወደ ቺካጎ ለመብረር ለቦርዲንግ ፓስ በተሰለፉበት ወቅት መጨረሻ ላይ ተሰልፎ የነበረው የእርምጃ ተወዳዳሪው ነገሮ አዱኛ በእርምጃ ወደ ኋላ አፈግፍጎ እሱም ከቡድኑ ተለየ፤ አራቱ አትሌቶች በተለያየ ግን በደንብ በተጠና የፊልም ስክሪፕት መሰል ክስተት ከአዲስ አበባው ጉዞ ቀሩ

እዚህ ላይ ግራ የሚያጋቡ ጥያቄዎች ይነሳሉ፤ አንደኛው አትሌቶቹም ሆኑ አሰልጣኞቹ ፓስፖርታቸውና ትኬታቸው ራሳቸው ጋር ስለነበር ለመቅረት ከፈለጉ ለምን ኤርፖርት ድረስ ሻንጣቸውን እየጎተቱ መጡ? እዛ የነበሩት አመራሮችስ ተራ በተራ ሲጠፉ ሆን ብለው በቸልተኝነት አልፈዋቸው ነው ወይስ ካቅማቸው በላይ ሆኖባቸው ነው? የሚቀሩ አትሌቶችና ባለሙያዎች እንደሚኖሩና ዝግጅት እያደረጉ እንደነበር አዲስ አበባ ያሉትም አሜሪካ የሄዱትም የፌዴሬሽኑ አመራሮች እያወቁ ለምን ትኩረት አልሰጡትም?

በነገራችን ላይ 17 አትሌቶችን ለመምራት የፅህፈት ቤቱ ሃላፊ ዶ/ር አመንሲሳ ከበደ፣ የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንትና ዋና ቡድን መሪዋ አትሌት መሰረት ደፋር፣ ምክትል ቡድን መሪዋና ስራ አስፈፃሚዋ አትሌት በላይነሽ ኦልጅራ፣ የቴክኒክ መሪው ኮማንደር ቶሌራ ዲንቃ በውድድሩ ቦታ ነበሩ፤ እነዚህ ሁሉ ባሉበት ከኩብለላው በተጨማሪ የሜዳሊያ ሽልማት ፕሮግራምን ረስተው ስልክ ሲደውል ባለመመለሳቸው አትሌቶቹ በሌላኛው ቀን ለመሸለም ተገደዋል፤ የህክምና ባለሙያ ባለመሄዱ ወድቀው ጉልበታቸውን የተጎዱ አትሌቶች ህክምና ሳያገኙ ቀርተዋል፤ ምግብ ያልተስማማቸው አትሌቶች ከነ ህመማቸው ሮጠዋል፤ የማሳጅ ባለሙያ ስላልሄደ አትሌቶቹ እርስ በእርስ ማሳጅ ሲደራረጉ ሰንብተዋል፤ ቡድኑ ከገባ በሁለተኛው ቀን የደረሰ አትሌት የሚቀበለው ሰው አጥቶ ፖርትላንድ የሚኖር ፍራኦል የሚባል የአትሌቲክስ ወዳጅ ተቀብሎት ማረፊያቸው ድረስ እስከመውሰድ ደርሷል፤ የኮሚኒኬሽን ባለሙያ ስለሌለ ከአዘጋጅ አካሉ ጋር ያለው ግንኙነት ተቋርጦ ዋጋ ተከፍሏል፤ ይህ ሁሉ ሆኖ ፌዴሬሽኑ ስኬታማ ነበርን የሚል አቋም ይዞ ሲሸላለም መዋሉ ያስደነግጣል፤ ከአትሌቶቹ በላይ አመራር ቦታ ላይ የተቀመጡት ሰዎች የሚሰሩት ፊልም ያሳቅቃል፤ ሌላው ሃገር ቢሆን በራስ ፍቃድ ስልጣን እስከመልቀቅ የሚደርስ ውሳኔ የሚያስወስን ቢሆንም የእኛዎቹ ገሚሱ በቡድን ተደራጅቶ፥ አንዱ በግል ትዕዛዝ እያስተላለፈ፥ ቀሪው በውጭ ጉዞ ፍቅር ተጠምዶ፥ ሌላው በብሄሩና በመንግስት ስር ተሸጉጦ፥ በካሜራ ፊት ግን እየተሳሳቁ ስለ ቀጣዩ አለም ሻምፒዮናና ኦሊምፒክ እቅድ ሲያወጡ ማየት ያማል፤ የአትሌቲክሱ መውረድ፥ የአትሌቶቹ እንባ፥ የባለሙያው ብሶት ለእነሱ ግድ አይሰጣቸውም!

በጋዜጠኛ ታምሩ ዓለሙ


Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2