በኢንዶኔዢያ በተከሰተ ከባድ ርዕደ መሬት ቢያንስ 38 ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቷ የአደጋ መከላከያ ድርጅት ገለጸ።
ቅዳሜ ዕለት ጠዋት በፍሎርስ ግዛት የተከሰተው ርዕደ መሬቱ በሬክተር ስኬል 7.7 ማግኒቲዩድ የተለካ ነው።
በፍርስራሽ ውስጥ የተቀበሩ ሰዎችን ለማውጣት የሚደረገው ፍለጋ እና የነፍስ አድን ሥራ የቀጠለ ሲሆን የሟቾች ቁጥርም እየጨመረ ነው።
በተፈጥሯዊ አደጋው ከሞቱት በተጨማሪም በርካታ ሰዎች የተለያየ መጠን ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በርዕደ መሬቱ እና ቀጥለው ባጋጠሙት በርካታ ንዝረቶች በክልሉ ያሉ ሕንፃዎችም ፈራርሰዋል።
የአገሪቷ ሚቲዮሮሎጂ እና ጂኦፊዚክስ ኤጀንሲ እንደገለፀው ርዕደ መሬቱ ፍሎርስ ደሴትን የመታው ቅዳሜ ጠዋት 1፡00 ሰዓት ላይ ሲሆን 15 ኪሎ ሜትር ጥልቀት አለው።
የመሬት መንቀጥቀጥ ጥልቅ ባልሆነ ሥፍራ ሲያጋጥም ብዙ ጉዳትን ያስከትላል።
ከርዕደ መሬቱ በኋላ በአካባቢው በ6.1 ማግኒቲዩድ የተለኩ ጠንካራ ንዝረቶችም ተሰምተዋል።
የርዕደ መሬቱ ማዕከል በሆነችው ግዛት በምዕራብ አቅጣጫ የምትገኘው ሩተንግ ከተማ ነዋሪ የሆኑት የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ዩሊያን ጁተታ ኢካሊያ “ እንደዚህ ዓይነት ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ተሰምቶኝ አያውቅም” ሲሉ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
“ልጆች እየዘለሉ የሚጫወቱበት ማስፈንጠሪያ (ስፕሪንግ) ላይ እንደሆንን ነበር የተሰማኝ ። በጣም አስፈሪ ነበር።” ብለዋል።
ወጣ ብሎ በሚገኘው ተራራማ ሥፍራ በደረሰው አደጋው ያጋጠመውን አጠቃላይ ውድመት ለመገምገምም ጊዜ ይወስዳል ተብሏል።
ሆኖም የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቶች 54 ቤቶች፣ አምስት የጤና መሠረተ ልማቶች፣ ሦስት የእምነት ተቋማት፣ ስድስት የመንግሥት ሕንፃዎች፣ የትምህርት ተቋም እና መጋዘን በከፍተኛ መጠን መውደማቸውን አመልክተዋል።










No comments yet.