ትያትር – ከስፖሌቶ፣ ጣሊያን

- Advertisement -
Sidebar AD

የጉዞ ማስታወሻ
ተስፋዬ እሸቱ (ረዳት ፕሮፌሰር)
ከጣሊያን፣

#Ethiopia | እንዴት ሰነበታችሁ?…
የትያትር ኤክስፐርመንትን ለመማር ጣሊያን ከመጣሁ አራት ቀን ሆነኝ።

የጋበዘኝ La MaMa Umbria International የተባለ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው። ተቋሙ በታዋቂዋ የትያትር ፈር ቀዳጅ ኤለን ስቱዋርት (Ellen Stewart) የተመሰረተ፤ ከዓለም ዙሪያ የሚመጡ የትያትርና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የሚገናኙበት፣ የሚማማሩበት፣ አዲስ ፈለግ የሚፈልጉበት፣ በጋራ የሚፈጥሩበትና ሐሳብ የሚለዋወጡበት ዓለም አቀፍ የፈጠራ መድረክ ነው።

እኔም ታዲያ ጣሊያን የተገኘሁት “ትያትርን አውቃለሁ” ብዬ ሳይሆን፣ ነፍሱን ይማረውና ጋሽ አባተ እንዳስተማረኝ፣ የትያትር ተማሪ ሆኜ ነው።

ትያትር የሚባለው ነገርም ይሄንኑ ይፈልጋል መሰለኝ፤ ምክንያቱም በተማርከው ቁጥር ያላወቅኸው ምን ያህል ብዙ እንደሆነ ይገልጥልሃል።

በእንደዚህ ዓይነት ዓለም አቀፍ የትያትር መድረክ ስሳተፍም የመጀመሪያ ጊዜዬ አይደለም። ሆኖም በተገኘሁ ቁጥር የሚገርሙኝ ነገሮች በጣም ብዙ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ለዛሬ አምስቱን ላንሳ።

1. ስነ ዘዴ (Methodology)

በመጀመሪያ ደረጃ ድንቅ ከሚሉኝ ነገሮች አንዱ የማስተማርና የመማር ስነ ዘዴያቸው ነው።

ምናልባትም እኮ የተነሳውን ጉዳይ አንድ ሺህ ጊዜ ሰምቼው ይሆናል። የሚቀርብበት መንገድ ግን ጉዳዩን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት ዓይነት ስሜት እንዲሰማኝ ያደርጋል።

በተጨማሪም ስነ ዘዴያቸው አእምሮን ብቻ ወደ እውቀት ፍለጋ የሚመራ አይደለም፤ አካል ይማራል፣ ስሜት ይሳተፋል፣ የማይነቃቃ አካል አይኖርህም። በዚህም ሁኔታ ልምድ ወደ እውቀት ይቀየራል።

ከምንም በላይ አይሰለችህም፤ እንደ ጨዋታ ነው የምትከታተለው።
ከዚህ አንጻር ምናልባት የብዙዎቻችን ፎቢያ የሆነውን የሂሳብ ትምህርት በእንዲህ ዓይነት ስነ ዘዴ ብንማረው ኖሮ፣ ስንት አንስታይን ይፈጠር ነበር? የትና የትስ እንደርስ ነበር አትሉም?

2. ከትንሽ ነገር ትልቅ ነገር መፍጠር

ከቀላል ነገር ተነስተው ትልቅ ሐሳብ የሚፈጥሩበት መንገድም ሁሌ ይገርመኛል።

ለምሳሌ፣ ከአንዲት ነጠላ ፎቶ ተነስተን የገነባነውን ትያትር ብታዩ ለማመን ትቸገራላችሁ።

አንዲት ፎቶ ብቻ!
ከዚያች ፎቶ ግን ገጸ ባህሪያት ይፈልቃሉ፣ ግጭት ይፈጠራል፣ ታሪክ ይገነባል፣ መድረክ ላይ ሕይወት ይፈጠራል፤ በቃ።

እኛ አገር አንድን ሲምፖዚየም ወይም ውይይት “ትልቅ” ለማድረግ የማንጠራው ዓለም አቀፍ ፈላስፋ፣ የማንጠቅሰው መጽሐፍ፣ የማናወሳስበው ነገር የለም።

እዚህ ግን ቀላል ነገር ይዘው ጥልቅ ባህር ውስጥ ይጥሉሃል፤ ጥልቀቱን ሳትፈራ ደስ እያለህ ትዋኛለህ። ከዚያም የሆነ ነገር ይዘህ ትወጣለህ።

ታዲያ ዋናው ጉዳይ ምንድን ነው?…

ታላቅ ሐሳብ ሁልጊዜ ውስብስብ መሆን የለበትም፤ አንዳንዴ የአንድ ነገር ታላቅነት በቀላልነቱ (Simplicity) ውስጥ ሊገነባ ይችላል። ያስማማ ይሆን?… አላውቅም።

3. ጊዜ!

ስለ ጊዜ አጠቃቀማቸውማ ምን ይባላል?… ጊዜን እኛ ቀለድንባት!…

ከሁለት ወር በፊት የተላከልንን ፕሮግራም አንዲት ደቂቃ ሳያዛንፉ እየተገበሩት ነው። “የእናቴ ቀሚስ ጠለፈኝ፣ የአባቴ ጭራ ዓይኔን አጠፋው” ወዘተ… ቦታ የለውም።

ፕሮግራሙ ሦስት ሰዓት ይጀመራል ከተባለ፣ ሦስት ሰዓት ይጀመራል። ቀልድ የለም፣ ወዳጀ!

“አሰልጣኙ ቁርሱን እየበላ ነው፣ እንጠብቀው”፣ “እከሌ አልመጣም”፣ “ወረቀቱ ስላልደረሰልን ጥቂት ደቂቃ እንጠብቅ” የሚባል ወዘተረፈ የለም።

እስኪ በእኛ አገር አውድ አስቡትና፣ “አራት ሰዓት ይጀመራል” ተብሎ አራት ሰዓት የተጀመረ ፕሮግራም ካለ አሳውቁኝ።
የገባኝ ነገር፣ ጊዜ ሰዓት ላይ የምናነበው ቁጥር ብቻ አይደለም።
ጊዜን ማክበር ማለት ሌላውን ሰው ማክበር ነው፤ ጊዜን ማክበር ማለት የሌላውን ሰው ሕይወት አለማባከን ነው።

4. ሙያን ማክበር

እየተሳተፍኩበት ባለው ፕሮግራም በቀን ስምንት ሰዓት ያህል እንሰራለን፤ አልተጋነነም።

ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተሰባሰቡትና በቀን ስምንት ሰዓት የሚሰሩትን (የምንሰራውን ልበል እንጂ) እነዚህን የትያትር ባለሙያዎች ሳይ፣ አንድ ነገር በግልጽ የገባኝ መሰለኝ።
ትያትር ለእነሱ ቀልድ አይደለም።
ይሰራሉ።

መሳሳት ብርቅ አይደለም፤ ይሳሳታሉ።

ይደግማሉ።

ይሞክራሉ።

እንደገና ሊሳሳቱ ይችላሉ።

እንደገና ይሞክራሉ።

ይደክማሉ፤ ግን አያቋርጡም።
ሙያቸውን ስለሚወዱ ያከብሩታል። ስለሚያከብሩትም ዋጋ ይከፍሉበታል።

“ሙያችሁ እንዲያከብራችሁ፣ መጀመሪያ እናንተ ሙያችሁን አክብሩ” የሚለውን ጥልቅ ሐሳብ በልባቸው ላይ የተነቀሱት ይመስላል።

እዚህ ላይ ጥያቄውን ወደ እኛ መመለስ ያስፈልጋል።
እኛ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ለሙያችን ምን ያህል ዋጋ እንከፍላለን?

ትያትር ወይም ፊልም ለመስራት ስንት ሰዓት እንለማመዳለን?
በቀን በትንሹ ስምንት ሰዓት ለሙያችን ለመስጠት ዝግጁ ነን?…
አላውቅም፤ መጠየቄ ነው።

5. ስልክ!

ቀደም ብዬ እንደነገርኳችሁ፣ መሳተፍ ከጀመርኩ አራት ቀን ሆኖኛል። በእነዚህ አራት ቀናት፣ ስልጠናው እየተካሄደ አንድም ስልክ ሲጮኽ አልሰማሁም፤ ማርያምን አልዋሸሁም።
ስልክ ስለሌላቸው፣ ወይም ማንም ስለማይደውልላቸው ግን አይደለም።

በቃ፣ ሥራ ነው የያዙት!
ሲሰሩ ይሰራሉ፤ ትኩረታቸው ሥራው ላይ ነው።
አቤት እኛጋ ቢሆን!…

አስቡት፤ የስልክ ጥሪውን…. ስልክ ይዞ ወጥቶ የሚያወራውን፣ ተመልሶ ሲገባ “የት ላይ ደረሳችሁ?” የሚለውን…

ለማንኛውም፣ ያኛው አገር የሰለጠነ፣ ያደገ ቢሆን አይደንቀኝም።
የእኛ ነገር ግን ይገርመኛል?!…

ብዙ ነገራችን ላይ ወለም ዘለም ያለበት መሰለኝ።
ምናልባት የሚያስፈልገን ትልቅ አብዮት ሳይሆን፣ ትንንሽ ነገሮቻችንን በትክክል መስራት ይሆን?… አላውቅም፤ መጠየቄ ነው።

ምን ትላላችሁ?
ሰላም እንሰንብት!





Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1