በአዲስ አበባ በቀን 60 ሺህ ሜትር ኪዩብ የመጠጥ ውሃ የሚያመርት እና ፍሳሽ የሚያጣራ ዘመናዊ ጣቢያ ተመረቀ

- Advertisement -
Sidebar AD

​#FastMereja I የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቀን 60 ሺህ ሜትር ኪዩብ ንፁህ የመጠጥ ውሃ የሚያመርት እና በቀን 20 ሺህ ሜትር ኪዩብ ፍሳሽ የሚያጣራ የኮዬ ፍሳሽ ዘመናዊ ማጣሪያ ጣቢያ ፕሮጀክቶችን መርቆ ለአገልግሎት ክፍት ማድረጉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።

​የከተማ አስተዳደሩ የንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሳደግ በቱሉ ጉዶ፣ ለገዳዲ ክፍል 2፣ በረከት የጋራ መኖሪያ አካባቢ፣ ቦሌ አራብሳ እና በሌሎች አካባቢዎች በርካታ የውሃ ጉድጓዶችን በማልማት ባለፉት አምስት ዓመታት የነበረውን የውሃ የማምረት አቅም ማሳደጉ ተገልጻል። በዚህም ከስድስት ዓመታት በፊት በቀን 525 ሺህ ሜትር ኪዩብ የነበረው የማምረት አቅም በአሁኑ ወቅት ወደ 910 ሺህ ሜትር ኪዩብ ማደጉ ተመላክቷል።

​በሌላ በኩል በከተማዋ የሚገኙ ወንዞች በፍሳሽ እና በደረቅ ቆሻሻ ይበከሉ የነበረበትን አሰራር ለመቀየር በተከናወኑ የፍሳሽ መሰረተ ልማት ማስፋፊያዎች ዘርፉ ላይ ከፍተኛ መሻሻል መታየቱ ተጠቅሷል። በፈረንጆቹ 2017 በቀን 20 ሺህ ሜትር ኪዩብ ብቻ የነበረው ፍሳሽ የማጣራት አቅም የአዲሱን ፕሮጀክት ጨምሮ በአሁኑ ወቅት ከ253 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ ማድረስ ተችሏል።

​አዲሶቹ ፕሮጀክቶች የነዋሪዎችን ጤና እና ንጽህና ከመጠበቅ ባለፈ የወንዞችን ብክለት በመቀነስ ለአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ተገልጻል። ለአጠቃላይ ፕሮጀክቱ ስኬት የዓለም ባንክ በብድር አቅርቦት፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የውሃ መገኛ አካባቢዎችን በትብብር በማልማት እንዲሁም አርሶ አደሮች መሬታቸውን ለልማት በመልቀቅ ድጋፍ ማድረጋቸው ተመላክቷል።






Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1