#Ethiopia | ታሪካዊዋ የእንጦጦ መንበረ ንግሥት ቊስቋም ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችበትን 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የሚያበስር መርሐ ግብር ነሐሴ 10 ቀን 2018 ዓ.ም. በተለያዩ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓቶች ተካሂዷል።
የደብሩ ዋና አስተዳዳሪ መልአከ ሣህል ቆሞስ አባ ፍቅረማርያም ምሕረቱ እንደገለጹት፣ የታላቁ በዓል አከባበር ከመጪው ኅዳር 6/2019 ዓ.ም. ዋዜማ ጀምሮ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በደመቀ ሁኔታ ይከበራል።
ከበዓሉ ጋር ተያይዞም እየጨመረ የመጣውን ምዕመናን ለማስተናገድና የደብሯን ታሪካዊ ደረጃ ለመጠበቅ የማስፋፊያና የእድሳት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በስነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአራዳና ጉለሌ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት አባ ገብረእግዚአብሔር ታደለ፣ አባቶች ያቆዩልንን እምነትና ታሪክ አስበልጦ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ገልጸው፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኦርቶዶክሳውያን ለደብሯ እድገት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ አባል ዶክተር ተስፋዬ ወርቁ በበኩላቸው የደብሯን አመሠረረት ሲያብራሩ፣ ቤተ ክርስቲያኗ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ አማካይነት ኅዳር 6 ቀን 1919 ዓ.ም. መተከሏን ገልጸዋል።
በወቅቱ በተሠራው መቃኞ ውስጥ ታቦተ ሕጉ ገብቶ በግብፃዊው ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ተባርኮ ቅዳሴ ቤቱ ተከብሯል።
በኋላም በቀዳማዊ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ አማካይነት መስከረም 25 ቀን 1925 ዓ.ም. የተጀመረው ግንባታ ግንቦት 24 ቀን 1925 ዓ.ም. ተጠናቅቆ ታቦቱ አሁን ወደሚገኝበት ህንፃ ገብቷል።
በ1928 ዓ.ም. የጣሊያን ወረራ ወቅት የተቋቋመው ማኅበረ ሰላምም እስከ አሁንም ድረስ በዕለተ መድኃኔዓለም በጸሎትና በጠበል ሕሙማን የሚፈወሱበትን አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
የማበሰሪያ መርሐ ግብሩን ተከትሎ የደብሩ ምዕራፈ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት አባላትና ካህናት በቅዱስ ጴጥሮስ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና በጌርጌሴኖን የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል በመገኘት ሕሙማንን ጎብኝተዋል።
የአዲስ አበባን ከተማ ቁልቁል በሚያሳይ ውብ ቦታ ላይ የምትገኘው የዚች ታሪካዊ ደብር የ100ኛ ዓመት በዓልን ምክንያት በማድረግ የሕንፃ እድሳት፣ የማስተር ፕላን ዝግጅት፣ የመጽሔትና የዘጋቢ ፊልም ማዘጋጀት፣ አውደ ርዕይና አውደ ጥናት ማካሄድ እንዲሁም ቅርሶችን የማሰባሰብ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሒሳብ ቁጥር 1000779660757 በመጠቀም ማበርከት ይችላሉ።
#entoto #kuskuammaryam #ethiopianorthodox #addisababanews #churchhistory
#getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa



Source: GetuTemesgen








No comments yet.