#Ethiopia | የኪውባው ታላቅ እና ዝነኛ ፕሬዝደንት ፊደል ካስትሮ፥ እ.ኤ.አ. ኦውገስት 13 ቀን 1926 የተወለዱበትን መቶኛ ዓመት የልደት በዓል አስመልክቶ፥ በኪውባ እና በዓለም ዙሪያ ሰሞኑን የተለያዩ የመታሰቢያ መርሐ ግብሮች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
“100 Years with Fidel” በሚል መሪ ቃል በኪውባ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ መታሰቢያዎች፣ ሲፖዚየሞች እና የፎቶ ኤግዚቢሽኖች ተከፍተዋል። በኒውዮርክ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት፣ በቪዬትናም እና በሌሎችም ሀገራት የሕይወት ታሪካቸውን እና ከሀገራቸው ጋር የነበራቸውን ግንኙነቶች የሚዘክሩ ዝግጅቶች እየተካሔዱ ነው። በሐቫና ከተማም ልዩ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች እና የምሁራን የታሪክ ምርምር ሥራዎች እየቀረቡ እንደኾነ የሚወጡ ዘገባዎች እየገለጹ ነው።
በዚህ ታላቅ የትውስታ ሰሙን ላይ ኾነን፣ የፊደል ካስትሮን እና የኢትዮጵያን ሕዝብ የጠበቀ ወዳጅነት እና ታሪካዊ ትብብር ማስታወስ የተገባ ይኾናል። በ1970ዎቹ የኢትዮጵያ አብዮት ውጣ ውረድ እና የህልውና አደጋ ጊዜያት፣ ፊደል ካስትሮ እና የኩባ መንግሥት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ቀዳሚ አጋዥ በመኾን የሐኪሞች፣ የቴክኒክ ባለሙያዎች እና የውትድርና ድጋፍ አበርክተዋል። የኢትዮጵያ እና የኩባ ወዳጅነት በደም እና በመንፈስ የተሣሠረ በመኾኑ፣ ዛሬም በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ የካስትሮ ስም ከነጻነት እና ከታማኝ ወዳጅነት ጋር ሲታወስ ይኖራል።
ከረዥሙ የፊደል ካስትሮ ታሪክ ዘወትር የፊልም ያህል የምትገርመኝን ይህችን ታሪክ እና ከእርሷ ጋር የተያያዘ አንድ የሙዚቃ ሥራን በዚህ ጽሑፍ ልተርክላችሁ ወደድኩ። ለነገር ኹሉ ሰበብ አይጠፋምና፥ ለዚህ ጽሑፍ ኹነኛው ሰበብ ሰሞኑን ከወዳጆቼ ከነ አገኘሁ አዳነ ጋር ያገኘነው፣ ትምህርቱን በኪውባ የተማረ ፈቃደ የተባለ ወዳጃችን ያጫወተን የኪውባ ትዝታ እና የፊደል ካስትሮ ውብ ሰብእና ወግ መኾኑን መግለጽ ሳይኖርብኝ አይቀርም። (ጽሑፉ ረዘም ቢልም፥ በትዕግሥት ታነቡታላችሁ የሚል እምነት አለኝ።)
————–o—————
እ.ኤ.አ. በ1959 የክረምት ወራት፣ “የካሬቢያን ዕንቍ” የምትባለዋ ኪውባ በዐዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ ውስጥ ነበረች። አምባገነኑን የፉልጀንሲዮ ባቲስታን ሥርዓት በመደምሰስ የሀገሪቱን መንግሥታዊ መሪነት የተረከበው ወጣቱ አብዮተኛ ፊደል ካስትሮ ሩዝ፣ በዓለም ፖለቲካ መድረክ ላይ በግዝፈት ብቅ አለ። እዚሁ ላይ ባለውለታውን ታላቁን ኤርኔስቶ ቼ ጉቪዬራን መርሳት አይቻልም።
የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት እና የደኅንነት ተቋሟ CIA በደጃፋቸው ሥር የተከሰተውን ይህንን የማርክሲስት ሌኒኒስት ርዕዮተ ዓለም አራማጅ መንግሥት እንደ ትልቅ የጸጥታ ስጋት ቆጠሩት።
ይህም ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት አንስቶ እስከ ምዕተ ዓመቱ መገባደጃ ድረስ የዘለቀውን የኃያላን ሀገሮች የቀዝቃዛ ጦርነት ውጥረት አባባሰው። የአሜሪካ የደኅንነት ባለሥልጣናት ካስትሮን ከሥልጣን ማስወገድ እና ሕይወቱን ማጥፋት እንደ ብሔራዊ የደኅንነት ጉዳይ ቅድሚያ ሠጥተው የሚንቀሳቀሱበት ኹነኛ ጉዳያቸው ኾነ።
በታሪክ መዛግብት እና በይፋዊ የCIA ሠነዶች እንደተረጋገጠው፣ በፊደል ካስትሮ ላይ የታቀዱ እና የተሞከሩ የግድያ ሙከራዎች ቁጥር 638 እንደደረሱ ተዘግቧል። CIA ካስትሮን ለማጥፋት የሳይንስ እና የቴክኖሎጂ ዳርቻዎችን የዳሰሱ እጅግ አደገኛ ዘዴዎችን ሞክሯል፦
• ካስትሮ ሲጋራ ወዳድ መኾኑን ሰበብ አድርገው፣ በመርፌ የተወጉ እና ገዳይ ንጥረ ነገሮች የተከተቡባቸው ሲጋራዎች፣
• በአካባቢው በሚገኙ ሰዎች እጅ የሚፈነዳ ልዩ ሲጋራ፣
• በUltra-lethal ባክቴሪያዎች እና ፈንገሶች የተበከለ የውኃ ዋና ልብስ፣
• የካስትሮን ጸጉር እና ዝነኛ መለያ ጺሙን እንዲረግፍ በማድረግ ገጽታውን በሕዝብ ዘንድ የተጠላ ለማድረግ የሚያስችሉ ኬሚካሎች፣
• በመርዝ የተበከሉ የምግብ እና የመጠጥ ዓይነቶች ይገኙበታል። ከእነዚህ ኹሉ የረቀቁ የግድያ ሙከራዎች ካስትሮ መትረፍ መቻሉ ብዙዎችን ሲያስደንቅ ኖሯል።
በዚህ ግዙፍ በሴራ የተከበበ የጂኦፖለቲካዊ ድራማ መሐል፣ የታሪክ ምሁራን እስካሁን ድረስ በስፋት ከሚያወሯቸው እጅግ አሳዛኝ እና ልብ አንጠልጣይ ትርኢቶች አንዱ የማሪታ ሎረንዝ (Marita Lorenz) እና የፊደል ካስትሮ የፍቅር ግንኙነት ነው።
ከጀርመናዊ አባት እና ከአሜሪካዊት እናት የተወለደቺው ማሪታ ሎረንዝ እ.ኤ.አ. በ1959 ዓ.ም. አባቷ ካፒቴን በነበረበት ግዙፍ እና ቅንጡ መርከብ ተሣፍራ ወደ ሐቫና ወደብ ደረሰች። በዚያም ዕጣ ፈንታ ከፊደል ካስትሮ ጋር አገናኛት።
በወቅቱ የ19 ዓመት ወጣት እና ማራኪ ውበት የነበራት ማሪታ ከካስትሮ ጋር በአንድ ዕይታ ፍቅር ውስጥ ወደቀች። የካስትሮ ማራኪ Charisma፣ አብዮታዊ ንግግሮች እና ለሀገሩ የነበረው ጽኑ አቋም ወጣቷን ማሪታ ሙሉ በሙሉ ማረካት። ፊደል ካስትሮም ለወጣቷ የነበረው ፍቅር የዋዛ አልነበረም። ኾኖም ይህ የፍቅር ግንኙነት የዘለቀው ለጥቂት ወራት ብቻ ነበር። ማሪታ ከካስትሮ ጸንሳ በነበረበት በዚህ ወቅት በደረሰባት ከባድ የጤና እክል እና ኪውባ ላይ በተከሰቱ ያልተጠበቁ ፖለቲካዊ ውዝግቦች ምክንያት ወደ አሜሪካ ትመለሳለች። በሚያሳዝን ኹኔታም ጽንሱ ተጨናግፎ የካስትሮ ልጅ እናት የመኾን ዕድልን አጣች።
ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ከተመለሰች በኋላ፣ ማሪታ ሎረንዝ የሕይወት መስመሯ ሙሉ በሙሉ ተቀይሮ ነበር ማለት ይቻላል። በጸረ ካስትሮ ፖለቲካ ለተጠመዱ ስደተኛ ኪውባውያን ሴራ ተታላይ ገጸ ባሕርይ ኾነች። በዚህ ወጥመድ ውስጥ እንዳለች፥ የCIA ወኪሎች ፊደል ካስትሮን በቀላሉ መቅረብ የምትችለው ብቸኛዋ ሰው ማሪታ እንደኾነች ተረዱ። ያለፈውን የፍቅር ግንኙነት እንደ መሣሪያ ለመጠቀም በማሰብም ወጣቷን ማሪታን አጠመዷት፣ አታለሏት። ጽንሱ የተጨናገፈው ካስትሮ በሠራው የሕክምና ምርመራ ተንኮል እንደኾነ አድርገው በሐሰት አሳመኗት።
CIA ካስትሮን እንድትገድል እጅግ ኃይለኛ የኾነ መርዝ (Botulinum toxin) የያዘ በካፕሱል መልክ የተዘጋጀ ንጥረ ነገር ሠጣት። መርዙ በካስትሮ ምግብ ወይም መጠጥ ውስጥ ተሰንጎ እንዲገባ በረቀቀ መንገድ ታቅዶ የተዘጋጀ ነበር። ማሪታ በወቅቱ በነበረባት የስሜት ቀውስ፣ በጽንሷ መጨናገፍ ምክንያት በነበረባት ኀዘን እና በCIA ከፍተኛ ጫና ተወጥራ ወደ ሐቫና ለመመለስ ተገደደች።
ማሪታ ሎረንዝ በድብቅ ሐቫና ገብታ ከፊደል ካስትሮ ጋር ተገናኘች። መርዙ በትንሽ ካፕሱል መልክ የተዘጋጀ ሲኾን፣ እሷም በመዋቢያ ቅባት መያዣ ውስጥ ደብቃው ነበር። ማሪታ በካስትሮ የግል መኖሪያ ክፍል ውስጥ ስትገባ፣ ጠላቶቹ አግኝተው ተልእኮ እንደሠጧት ለማወቅ ጊዜ አልወሰደበትም። ምናልባት የመረበሽ እና ያለመረጋጋት ስሜት ስላየባት ሊኾን ይችላል፣ አንድ ክፉ ተልእኮ ተሸክማ እንደመጣች ጠረጠረ። ነገር ግን ካስትሮ የጠላትነት ስሜት ወይም ጥርጣሬውን የሚያጋልጥ ቁጣ መሣይ ነገር አላሣየም። እንዲያውም በጥልቅ ስሜት ተመለከታት።
ካስትሮ በሰከነ መንፈስ የራሱን ሽጉጥ ከወገቡ አውጥቶ በእጇ ላይ አስቀመጠላት። “ልትገድይኝ መጥተሻል አይደል? ይህንን ሽጉጥ ውሰጂና ግደይኝ፣ እኔን የመግደል ሙሉ መብት ያለው CIA ሳይኾን አንቺ ነሽ!” አላት።
ካስትሮ ይህንን ድርጊት የፈጸመው በከፍተኛ ድፍረት እና ማሪታ እሱን ለመግደል የህሊና ዝግጅት እንደሌላት፣ አሁንም እውነተኛ ፍቅር በውስጧ እንዳለ እርግጠኛ ኾኖ ነበር። ማሪታ በዚያች ቅጽበት የጥፋተኝነት ሸክሟን መሸከም አቅቷት፣ ዕንባዋን ማቆም አቅቷት በጸጸት ስቅስቅ ብላ አለቀሰች። እግሩ ላይ ወድቃ ይቅርታ ጠየቀችው። ካስትሮም ይቅርታ አደረገላት፤ የመጨረሻውን የፍቅር ጊዜም አብረው አሳለፉ።
ማሪታ ከዚህ ክስተት በኋላ ኪውባ ውስጥ ብዙም አልቆየችም። ወደ አሜሪካ ተመለሰች። የካስትሮን ግድያ ባለማሳካቷ ምክንያት ሕይወቷ አደጋ ውስጥ በመግባቱ፣ ሌሎች የስለላ ድርጊቶች ውስጥ በመግባት የተወሳሰበ ሕይወት ብታሳልፍም፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሕይወት ዘመኗ ሙሉ ለካስትሮ ልዩ ቦታ እንደነበራት እና የትኛውንም ሌላ ወንድ ከእሱ ጋር ማወዳደር እንዳልቻለች በተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ቃለ መጠይቆቿ ላይ ተናግራለች። ማሪታ ሎረንዝ ይህንን ታሪክ በራሷ ዐንደበት በወቅቱ በነበሩ የተለያዩ ዘጋቢ ፊልሞች እንደ «My Lover, My Killer» በመሣሠሉት ላይ በዝርዝር መስክራለች።
ማሪታ ሎረንዝ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው እ.ኤ.አ. በ2019 ነበር። ፊደል ካስትሮም እጅግ በርካታ የCIA የግድያ ሙከራዎችን አልፎ፣ በዕድሜም ጠግቦ (በ90 ዓመት ዕድሜው) በ2016 ዓ.ም. ከእርሷ ሦስት ዓመታት ቀድሞ ማረፉ ይታወሳል።
ይህንን ፍቅርን እና የፖለቲካ ትግልን ያዘለ ታሪክ ስናሰላስል፣ የኪውባው ድንቅ አቀንቃኝ የኢብራሂም ፌሬር «Dos Gardenias» ሲል ያዜመውን ድንቅ የፍቅር ሙዚቃ አብረን ለማስታወስ እንገደዳለን። ሙዚቃው ስለ ናፍቆት እና ልብን ስለሚሰብር የፍቅር ጸጸት የሚናገር፣ የማሪታ እና የካስትሮን ፍቅር እንዲሁም የማሪታን ጸጸት የማስታወስ ኃይል ያለው ሙዚቃ ነው።
* በዚሁ አጋጣሚ ኢብራሂም ፌረርን ብናስታውሰው ምን ይለናል?
ኢብራሂም ፌረር እ.ኤ.አ በ1927 ተወልዶ፣ በ2005 ዓ.ም. ይህችን ዓለም የተሰናበተ፣ በኩባ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ እጅግ አስደናቂ እና ልብ የሚነካ የሕይወት ታሪክ ያለው ድምፃዊ ነው። ፌረር የተወለደው በሳንቲያጎ ከተማ ሲኾን፣ ገና በ12 ዓመቱ ወላጆቹን በሞት በመነጠቁ ሕይወትን ለማሸነፍ በጎዳናዎች ላይ ዘፍኗል፤ ሎተሪ አዙሯል፣ እንደ ታላቁ ድምፃዊያችን እንደ ማሕሙድ አሕመድ ሊስትሮነትን ጨምሮ የተለያዩ የጉልበት ሥራዎችን ሠርቷል።
ከ1950ዎቹ ጀምሮ ከተለያዩ ታዋቂ የኪውባ የሙዚቃ ቡድኖች ጋር ቢዘፍንም፣ ድምፁ ለስላሳ እና ረጋ ያለ በመኾኑ እንደ ዋና (ሶሎ) ድምጻዊ ሳይኾን እንደ አጃቢ (backing vocalist) ብቻ ይታይ ነበር።
በጥረቱ ልክ በድምፃዊ ደረጃ ባለመታየቱ ተሰላችቶ፣ በ1980ዎቹ መጨረሻ ከሙዚቃው ዓለም ሙሉ በሙሉ በመውጣት፣ ወደ ልጅነቱ የሊስትሮነት ሥራ ተመለሰ።
ነገር ግን፥ በ1990ዎቹ አጋማሽ፣ ፌረርን ከጎዳና ወደ ስቱዲዮ የሚመልስ አንድ ክስተት ተፈጠረ። አሜሪካዊው ጊታሪስት ራይ ኩደር (Ry Cooder) እና ኪውባዊው ሙዚቀኛ ሑዋን ደ ማርኮስ ጎንዛሊየዝ፥ ለዐዲስ የሙዚቃ አልበም ፕሮጀክታቸው ቀደምት የኩባ ሙዚቀኞችን ሲፈልጉ፣ ፌረርን በሐቫና ጎዳናዎች ላይ አልባሌ ሰው ኾኖ አገኙት። በዚህ ጊዜ ኢብራሂም ፌረር ዕድሜው 70 ኾኖ ነበር።
በዚህ ልዩ አጋጣሚ በ70 ዓመቱ ወደ ስቱዲዮ የተመለሰው ፌረር፣ እ.ኤ.አ. በ1997 በወጣው Buena Vista Social Club አልበም አማካኝነት የዓለም አቀፍ ዝና ባለቤት ኾነ፤ የግራሚ (Grammy) ሽልማትንም አሸነፈ።
በዚህ የቡዌና ቪስታ ሶሻል ክለብ አልበም ውስጥ የተካተተው «Dos Gardenias» (ኹለቱ አበባዎች) የተሰኘው ሙዚቃ፣ በ1945 በኩባዊቷ ደራሲና አቀናባሪ ኢሶሊና ካሪዮ (Isolina Carrillo) የተጻፈ የላቲን አሜሪካ የታወቀ የፍቅር ሙዚቃ ነው። ዘፈኑ በብዙ የኪውባ ድምፃውያን ቢቀነቀንም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመጨረሻውን ጥግ ዕውቅና ያገኘው ግን፣ በኢብራሂም ፌረር ጥልቅ እና ስሜታዊ ድምፅ ተዘፍኖ፥ በቡዌና ቪስታ ሶሻል ክለብ አልበም ውስጥ ከተካተተ በኋላ ነው።
በዘፈኑ ውስጥ ያለው ሐሳብ፥ ለፍቅረኛው ኹለት የጋርዴኒያ አበቦችን የሠጠ አንድ ወጣትን ያስታውሳል። እነዚህ አበቦች ተምሣሌታዊ መልእክት አላቸው። አበቦቹ፥ ወጣቱ ምን ያህል እንደሚወዳት እና እንደሚያከብራት ይነግሯታል። ዘፈኑ በኹለቱ አበቦች በኩል እንዲህ ይላል፦
“እነዚህ አበቦች ሕይወት አላቸው፣ ነገር ግን በፍቅራችን መሐል ክኅደት ከተፈጠረ አበቦቹ ወዲያውኑ ይደርቃሉ፤ ያኔ ፍቅራችን እንደሞተ በእርግጥ ታውቂያለሽ።”ይላል።
«Dos Gardenias» የተሠራበት የሙዚቃ ዘይቤ ቦሌሮ (Bolero) ይባላል። ቦሌሮ ደግሞ፥ የኪውባ ረጋ ያለ እና ፍቅር ቀመስ መልእክት የሚሸከም የሙዚቃ ሥልት ነው። ከኢብራሂም ፌረር አጨዋወት እና ስሜታዊ ድምፅ ጋር ተዋሕዶ ስንሰማው፣ ሙዚቃው አሳዛኝ ናፍቆት እና ጸጸት ያዘለ ስሜት ተሸክሞ እናገኘዋለን።
የፊደል ካስትሮ 100ኛ ዓመት ልደት መታሰቢያ ሲከበር፣ ከኢትዮጵያ ጋር የነበረው ጽኑ ወዳጅነት፣ ከማሪታ ጋር የነበረው የፍቅር ታሪክ፣ እንዲሁም የኢብራሂም ፌረር «Dos Gardenias» የናፍቆት ዜማ የኪውባን ታሪክ በልዩ ጥልቀት እና ውበት በውስጣቸው ይዘው ለትውስታ ከፊታችን ይደቀናሉ።
ሰርጸ ፍሬስብሐት
ማስታወሻ
————-
የኢብራሂም ፌረርን “Dos Gardenias” ሙዚቃ ማዳመጥ ከፈለጉ ይህንን Link ይክፈቱት። https://youtu.be/S4ZqO5Zq9QY?si=izsradXZEKnlD4sk
Source: GetuTemesgen








No comments yet.