የጉዞ ማስታወሻ
ተስፋዬ እሸቱ (ረዳት ፕሮፌሰር)
ከጣሊያን፣ ስፖሌቶ
#Ethiopia | ስፖሌቶ ካየኋቸውና እጅግ ካስደነቁኝ ታሪካዊ ስፍራዎች አንዱ የስፖሌቶ የሮማውያን ትያትር (Teatro Romano di Spoleto) ነው።
ትያትሩ በ1ኛው ክፍለ ዘመን ዓ.ዓ. (1st century BC) የተገነባ ነው። ልብ አድርጉ፤ በዚያ ዘመን ሙሶሎኒ አልተፈጠረም። ኢትዮጵያችን ግን ነበረች፤ ስሟም ገናና ነበር። ታዲያ፣ ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ ታሪክ ያለውን ይህን ትያትር በአካል ማየት ለእኔ ልዩ ስሜት ነበረው።
ከሁለት ሺህ ዓመት በፊት ሰዎች እዚህ፣ በእነዚህ የድንጋይ መቀመጫዎች ላይ ተቀምጠው ምን ይመለከቱ ነበር? ያኔ እዚህ ምን ይሰማ፣ ይታይ ነበር? የተዋንያኑ ድምፅ? የተመልካቹ ጫጫታ? ወይስ ትዕይንቱን በጸጥታ የሚከታተል የሰዎች ስብስብ?
የዚያ ዘመን ሳቅስ ምን ይመስል ነበር? እንደ እኛ ጮክ ብለው ይስቁ ነበር? በአሳዛኝ ትዕይንት ልባቸው ተነክቶ ያለቅሱ ነበር? ተዋንያኑ ድንቅ ትወና ሲያቀርቡ ያጨበጭቡላቸው ነበር? ወይስ ደስታቸውንና አድናቆታቸውን ከእኛ በተለየ መንገድ ይገልጹ ነበር? ትዕይንቱ ሲያልቅስ ሰዎቹ ምን እያሰቡ ከዚህ ቦታ ይወጡ ነበር? ያዩትን ትዕይንት እያወሩ ወደ ቤታቸው ይጓዙ ነበር?…. እነዚህና ሌሎች ብዙ ጥያቄዎች በአእምሮዬ ይመላለሳሉ።
ምናልባትም የዚህ ጥንታዊ ትያትር አስደናቂነት ምስጢር ይህ ይሆናል። አፍጥጠህ ስትመለከት የድንጋይ መቀመጫዎቹ ዝም ያሉ ናቸው፤ በምናብህ ግን ከሁለት ሺህ ዓመት በፊት ወደነበረው መድረክ ይወስዱሃል። የዚያን ዘመን ተዋናይ እንድታስብ፣ ተመልካቹን እንድትፈልግ፣ በሁለቱ መካከል የነበረውን ግንኙነት በምናብህ እንድትገነባ ያደርጉሃል። ይገርማል!
ከታሪክ ማኅደር የምናገኘው ሐቅ ደግሞ ፣ የሮማውያን ትያትር የመዝናኛ ስፍራ ብቻ እንዳልነበረ ይነግረናል፤ ሕዝብ የሚሰባሰብበት፣ ታሪኮች የሚነገሩበት፣ የዘመኑ እሴቶችና ማኅበራዊ ሕይወት በመድረክ ላይ የሚገለጡበት ሕዝባዊ ስፍራ ነበር።
ከዚህ ጥንታዊ መድረክ በኋላ Teatro Nuovo Gian Carlo Menottiን የማየት ዕድል አገኘሁ። በ1854 ግንባታው ተጀምሮ በ1864 የተከፈተው ይህ የ19ኛው ክፍለ ዘመን ትያትር፤ ከጥንታዊው የሮማውያን ክፍት መድረክ ወደ ጣሊያናዊው የትያትር ቤት አወቃቀር የተደረገውን ረጅም የትያትር ጉዞ በአንድ ከተማ ውስጥ እንድናይ ያደረገ ነው። ስለ ሥነ ሕንፃውማ ምኑ ተነግሮ ያልቃል! ውበቱንና ግርማ ሞገሱን ሳይ፣ “በአገሬ በሆነ!” ብዬ ተመኘሁ።
በእነዚህ ሁለት ዘመናት መካከል የመድረኩ ቅርጽ፣ የተመልካች አቀማመጥ፣ የተዋናይና የተመልካች ግንኙነት ተለውጧል፤ የሰው ልጅ ታሪኩን ለሌላው የመናገር፣ የሌላውንም ታሪክ የመስማትና የመናገር ፍላጎቱ ግን አልቆመም፤ አልተለወጠምም። ምናልባት የትያትር ምስጢርም ይህ ይሆናል።
የዚህን ታሪካዊ ጉዞ ማሳረጊያ የSpoleto Black Box Theatreን በመጎብኘት ተጠናቀቀ። በ2010 የተገነባው ይህ ቦታ፣ ከጥንታዊው የሮማውያን ትያትርና ከ19ኛው ክፍለ ዘመን Teatro Nuovo በተለየ፣ የመድረኩና የተመልካቹ አቀማመጥ እንደ ሥራው ፍላጎት ሊቀየር የሚችልበት፣ አዳዲስ የትያትር ቅርጾችና የክዋኔ ሙከራዎች (theatrical experiments) የሚካሄዱበት የዘመናችን የፈጠራ ላቦራቶሪ ነው።
በአንድ ከተማ ውስጥ ያሉት እነዚህ ሦስት መድረኮች፣ ትያትር ትውልድን ከትውልድ የሚያገናኝ ድልድይ ለመሆኑ ሕያው ማስረጃዎች ናቸው።በዚህም የጥንቱ ሮማዊ ትውልድ ታሪኩን በክፍት መድረክ ላይ ተርኳል፤ የ19ኛው ክፍለ ዘመን ትውልድ ለትያትር አዲስ የሕንፃና የውበት ቅርጽ ሰጥቶታል፤ የዛሬው ትውልድ ደግሞ በBlack Box ውስጥ የተለመዱ የትያትር ድንበሮችን እየፈተነ አዳዲስ የክዋኔ ቋንቋዎችን ይፈጥራል። መድረኩ ተለውጧል፤ ትውልዱ ተለውጧል፤ ታሪክን የመናገር የሰው ልጅ ፍላጎት ግን አልተለወጠም።
በዚህ ትርጉም ትያትር “ሕያው ማኅደረ ታሪክ” (living archive)ነው ማለት እንችላለን። ትያትርን ሕያው ማኅደር የሚያደርገው ያለፈውን ስለሚያስቀምጥ ብቻ አይደለም፤ እያንዳንዱ አዲስ ትውልድ የቀደመውን ተቀብሎ እንደገና ህይወትን ስለሚተረጉም፣ የራሱን አዲስ ነገር ጨምሮ ለሚቀጥለው ስለሚያስተላልፍ ነው።
ትያትር ታሪክን በመጻሕፍትና በሙዚየሞች እንደሚቀመጥ ቁስ ብቻ አድርጎ አይመለከትም፤ በሰው አካል፣ በድምፅ፣ በእንቅስቃሴ፣ በቦታና በተመልካች ፊት በየጊዜው እንደገና ሕያው ያደርጋል። ያለፈውን ወደ አሁን ያመጣል፤ አሁን ያለውንም ለወደፊቱ በተግባር ያስተላልፋል።
ስለዚህ ለእኔ ስፖሌቶን መጎብኘት ሦስት የትያትር ሕንፃዎችን ማየት ብቻ አልነበረም። ከ1ኛው ክፍለ ዘመን ዓ.ዓ. ወደ 19ኛው ክፍለ ዘመን፣ ከዚያም ወደ 21ኛው ክፍለ ዘመን፤ ከRoman Theatre ወደ Teatro Nuovo፣ ከTeatro Nuovo ወደ Black Box ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ የተጓዘውን የትያትር ታሪክ በእግሬ ተጉዤ እንዳነበብኩት ዓይነት ስሜት ነው የሰጠኝ።
በመጨረሻም ምን ለማለት ነው…
ሕንፃዎቹ ይለወጣሉ፤ ዘመናት ያልፋሉ፤ ትውልዶች ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ፣ ይተካሉ፤ ትያትር ግን የአንዱን ትውልድ ድምፅ ለሌላው እያስተላለፈ፣ ትውልድን ከትውልድ ማገናኘቱን ይቀጥላል።
ቸር ዋሉ!
La MaMa Umbria International:
https://lamama.org/la-mama-umbria-international/












No comments yet.