#Ethiopia | የጉራጌን ህዝብ ስነ-ልቦና፣ የህይወት ፍልስፍና እና ባህላዊ ክህሎቶች በሰፊው የሚያስተዋውቅ አዲስ ታሪካዊ መጽሐፍ ተመረቀ
በደራሲ ነጋሽ በቀና የተዘጋጀው እና የጉራጌን ማህበረሰብ ስነ-ልቦናዊ መዋቅር፣ የአኗኗር ዘይቤ ፍልስፍናዎች እንዲሁም ባህላዊ ፈጠራዎችን በጥልቀት የሚዳስሰው የ መጽሐፍ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በታላቅ ድምቀት ተመርቋል።
በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ የታደሙ የተለያዩ ምሁራን፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደገለጹት መጽሐፉ ከማህበረሰቡ ህይወት፣ ታሪክና ማንነት ጋር ጥልቅ ቁርኝት ያለው ታላቅ የምርምር ማህደር ነው። መሰል የህዝብን ባህልና እሴት የሚያስተዋውቁ ስራዎች ተሰንደው ለቀጣዩ ትውልድ እንዲሸጋገሩ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ደራሲ ነጋሽ በቀና እንደተናገሩት መጽሐፉ ማህበረሰቡ ውስጣዊ ማንነቱን ይበልጥ እንዲንከባከብ፣ ራሱን እንዲገልጽ እና መልካም የህይወት እሴቶቹን ለሌሎች እንዲያስተላልፍ ለማስቻል የተዘጋጀ ነው።
ከ1978 ዓ.ም ጀምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሲሰሩ የቆዩት ደራሲው፣ ጥናታዊ መረጃዎችን በማከማቸት ያዘጋጁት ይህ መጽሐፍ በቅርቡ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ለንባብ እንደሚበቃም አበስረዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ወንድወሰን አውላቸው እና የመጽሐፉ ምረቃ አስተባባሪ አቶ ክፍሌ ሰብጋዘ በበኩላቸው፣ መጽሐፉ የጉራጌን ተገልጦ ያልተነበበ ማንነት፣ የኑሮ ጥበብ እና ስነ-ልቦና ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ፣ ባህል ከመጥፋት የሚታደግና ለጥናትና ምርምር የሚጠቅም ንድፈ-ሀሳብ የያዘ መሆኑን ገልጸዋል።
የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሀላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ እና ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በበኩላቸው ወጣቶች የማንበብ ልምዳቸውን በማሳደግ የአካባቢያቸውን ባህል ማወቅ እንዳለባቸው ገልጸው፣ መጽሐፉ ለትውልድ የሚተላለፍ ትልቅ የታሪክ አሻራ መሆኑን ገልጸዋል።
#ጉራጌሲገለጥ #ነጋሽበቀና #የመጽሐፍምረቃ #ባህልእናታሪክ #ኢትዮጵያ #GurageSigelet #EthiopianLiterature #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa

Source: GetuTemesgen









No comments yet.