#Ethiopia | በናይጄሪያ ኢሞ ግዛት በሚገኘው ፌደራል ፖሊቴክኒክ ት/ት ቤት የፋርማሲዩቲካል ቴክኖሎጂ ተማሪ የሆነው የ23 ዓመቱ ፕሮሚስ የትምህርት ፍጻሜውን ከጓደኞቹ ጋር በደስታ በማክበር ላይ ሳለ ያልተጠበቀ ክስተት አስተናግዷል።
ተመረቂዎቹ በነጭ ቲሸርታቸው ላይ የመልካም ምኞት መግለጫዎችን በመጻፍና በሙዚቃ ታጅበው ደስታቸውን ሲገልጹ በነበሩበት ወቅት የፕሮሚስ እናት ወይዘሮ ቺንየሬ ፍየል እየጎተቱ ወደ አከባበሩ ስፍራ ብቅ አሉ።
እናትየው ያዘጋጁለትን ይህን ድንገተኛ ስጦታ ሲመለከት ተማሪው ከመደነቁ ባሻገር የማያውቀው ስሜት ውስጥ መውደቁን ገልጻል።
ይህ የደስታ ቅጽበት በቪዲዮ ተቀርጾ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከተሰራጨ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ የብዙዎችን ቀልብ በመሳብ በይነመረብ ላይ ገኗል።
በደቡብ ምስራቅ ናይጄሪያ በሚኖረው የኢግቦ ብሔር ባህል መሠረት ፍየል በስጦታነት ማበርከት ከፍተኛ ክብርን፣ ምስጋናን እና መልካም ምኞትን የሚያሳይ ትልቅ ዋጋ ያለው ትውፊት ነው።
እናት ቺንየሬ ልጃቸው ከተለያዩ መጥፎ ድርጊቶችና አላስፈላጊ ቡድኖች ታቅቦ ትምህርቱን በስኬት ካጠናቀቀ ሽልማት እንደሚያገኝ የገቡለትን ቃል ለመጠበቅ ሲሉ 120,000 ናይራ ($88) በማውጣት ስጦታውን አዘጋጅተውታል።
እናት ይኸንኑ ስጦታ ይዘው ከሚኖሩበት ገጠር መንደር ከአንድ ሰዓት በላይ መንገድ በመጓዝ ነበር በቦታው የተገኙት።
በአሁኑ ወቅት ይህ ፍየል በተማሪዎች መኖሪያ አካባቢ በነጻነት የሚንቀሳቀስ ከመሆኑም በላይ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።
ፕሮሚስ ፍየሉን ፈጽሞ እንደማያርደውና እንደውም የቤት እንስሳ አድርጎ እንደሚያኖረው የተናገረ ሲሆን ፍየሉ የጥብስ ሩዝ መመገብ እንደሚወድና አብሮት በመኪና ወደ ገበያ ማዕከል ጭምር እየተጓዘ ከሰዎች ጋር ፎቶ እንደሚነሳ ገልጻል።
ፕሮሚስ ተወዳጅነት ያተረፈውን ይህን ፍየል ወደፊት ሴት ፍየል በመግዛት የማርባት እቅድ እንዳለውም አክሎ ገልጻል።
በያፌት ገ/ህይወት
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu
Source: GetuTemesgen









No comments yet.