የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ፣ ከኢራን ጋር ያላትን ሁሉንም የንግድ እንቅስቃሴዎች፣ የንግድ ልውውጦች እና የገንዘብ ዝውውሮች ሌላ መግለጫ እስኪሰጥ ድረስ አገደች።
አገሪቱ ይህን እርምጃ የወሰደችው፣ ሁለት ከኢራን የተተኮሱ ባሌስቲክ ሚሳዔሎች የገልፍ የባሕር ላይ ትራፊክን ዒላማ ማድረጋቸውን ካሳወቀች በኋላ ነው።
ረቡዕ ዕለት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ የሆነው ይህ ውሳኔ፣ በቀጣናው እየተስፋፋ ያለው ወታደራዊ ግጭት በኢራን እና በባሕረ ሰላጤው ጎረቤቶቿ መካከል ባለው የኢኮኖሚ ግንኙነት ላይ እየተንፀባረቀ ስለመሆኑ የቅርብ ጊዜ ማሳያ ነው።
ይህ እገዳ በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ሰላም እና ጸጥታ ላይ ተፅእኖ ያሳደሩ ለውጦችን ተከትሎ የተወሰነ መሆኑን አቡ ዳኢ አስታውቃለች።
ከኢራን ተተኮሱ ከተባሉት ሁለት ሚሳዔሎች ውስጥ አንዱ በኢሚሬትስ ክልል ውስጥ ባለ የውሃ አካል ላይ የወደቀ ሲሆን ሌላው ደግሞ ከውሃ ክልሏ ውጭ ባለ ውሃ ላእ መውደቁን ሚኒስቴሩ ገልጿል። ምንም እንኳን ሚሳዔሎቹ መርከብ ባይመቱም፣ በባሕር ትራፊክ ላይ ያነጣጠሩ ናቸው ተብሎ ተገምግሟል።
ኢራን በተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ የቀረበባትን ክስ አስተባብላለች። የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ፣ ክሱን “መሠረተ ቢስ” ነው ብለዋል። ከ“መልካም ጉርብትና” ጋር የሚቃረኑ መሆናቸውንም የገለፁት ቃል አቀባዩ፣ የቀጣናው አገራት በቴህራን ላይ ከሚሰነዘሩ “መሠረተ ቢስ” ክሶች እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
ክስተቱ “በሀሰተኛ ባንዲራ” የሚደረግ እንቅስቃሴ ሊሆን እንደሚችል በመጥቀስ፣ የቀጣናውን ፀጥታ ለመገምገም የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ፣ በኢራን የተፈረጁ የአሜሪካ እና የእስራኤልን “የተንኮል ድርጊቶች” ግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለበት ገልፀዋል።
ይህ አለመግባባት የተፈጠረው፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በግጭቱ እና በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ካለው የመርከብ እንቅስቃሴ መስተጓጎል ጋር የተያያዙ ችግሮችን እየተጋፈጠች ባለችበት ወቅት ነው።
የዩኤኢ የአሁኑ እርምጃ፣ ሁለቱ አገሮች የጠለቀ የኢኮኖሚ ግንኙነት ያላቸው እደመሆኑ ከዲፕሎማሲያዊ አለመግባባት ያለፈ መዘዝ ሊኖረው የሚችል ነው።











No comments yet.