ተከሳሽ አሳየው በዛብህ የፍቅር ጓደኛው በነበረችው ግለሰብ ላይ የመግደል ሙከራ ወንጀሉን የፈጸመው ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ/ም በየካ ክ/ከተማ በድሮው ወረዳ 13 የካ አባዶ አካባቢ ነው።
ተከሳሹ ለዓመታት የፍቅር ጓደኛው አድርጋው ከነበረችው የግል ተበዳይ ጋር ባለ መግባባት ተለያይተው የቆዩ ሲሆን የራሷን የተሻለ ህይወት በመጀመሯ የቅናት መንፈስ ያድርበታል። በዚህም ሳያበቃ ወደ መኖሪያ ቤቷ ሄዶ ሊያናግራት ሲሞክር የግል ተበዳይ አልፈልግህም ከህይወቴ ውጣ ስትለው በቦክስ የጀመረውን ድብደባ የሽንኩርት መክተፊያ ቢላዋ በማንሳት ከጎኗ እና ከእጇ ላይ በመውጋት ጉዳት አድርሶባት መሰወሩን የየካ ክ/ከተማ ዋና ፖሊስ ዋና መምሪያ ገልጿል።
ተከሳሹ የወንጀል ድርጊቱን እንደፈጸመ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጥቆማ የደረሰው ፖሊስ ግለሰቡን በቁጥጥር ስር አውሎ በሰውና በህክምና ማስረጃ የተደገፈ መዝገብ በማደራጀት ለአቃቤ ህግ ማስረከቡን ዋና መምሪያው አስታውሷል።
ተከሳሽ በወቅቱ ዋስትና ተፈቅዶለት ጉዳዩን በውጪ ሆኖ እንዲከታተል ቢደረግም በፍርድ ቤት ቀጠሮው ቀን ሳይገኝ ቀርቷል።
ተጣርቶ የቀረበለትን የምርመራ መዝገብ የተመለከተው በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ቦሌ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ጥቅምት 3 ቀን 2015 ዓ/ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ አሳየው በዛብህን በሌለበት በ7 ዓመት ከ8 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ አስተላልፎበታል።
ፍ/ቤቱ ፖሊስ ተከሳሹን ይዞ ለማረሚያ ቤት እንዲያስረክብ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ፖሊስ ብርቱ ክትትል እና ማፈላለግ ሲያደርግ ቆይቶ ከ3 ዓመታት በኋላ ነሐሴ 8 ቀን 2018 ዓ/ም በቁጥጥር ስር አውሎ ለማረሚያ ቤት ማስረከቡን የየካ ክ/ከተማ ዋና ፖሊስ ዋና መምሪያ ገልጿል፡፡
ፍግለሰቦች በወንጀል ተከሰው በፍ/ቤት ዋስትና ተፈቅዶላቸው ጉዳቸውን ውጪ ሆነው እንዲከታተሉ ሲደረግ ተከሳሾች የዋስትና መብታቸውን ተጠቅመው የቅጣት ማቅለያ በማቅረብ በህግ አግባብ መጨረስ አለባቸው ያለው የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ወንጀል ፈጽመው በፍ/ቤት ህጋዊ ቅጣት ተወሰኖባቸው ከህግ ለማምለጥ ተደብቀው የሚኖሩ ግለሰቦችን ህብረተሰቡ ለፖሊስ አሳልፎ ለመስጠት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስቧል፡፡
Addis Ababa police
Source: Yeneta Tube









No comments yet.