የሰለሞን ደነቀ “ስርቅታዬ” ዜማ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ የተሻገረበት አዝናኝ ትዝታ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | ዜማ የትናንት የታሪክ ገጾችን ገልጦ ትዝታን ወደ አእምሮ የሚ መልስ ድንቅ የጥበብ ስራ ነው።

በደስታ ስሜት እያንሳፈፈ ያለፈውን ጊዜ ያስታውሳል። የዛሬው ህይወታችን በትናንት ታሪካችን የተሰራ መሆኑን ያሳያል፤ በጊዜ ሂደት ያሳለፍናቸውን ውብ አጋጣሚዎች፣ የሳቅናቸውን የሳቅ ጊዜያትና የለበስናቸውን አልባሳት ሳይቀር በህሊናችን ድጋሚ ህያው አድርጎ ያቆማቸዋል።

የዓውደ ዓመት ደስታ ያለ እነዚህ ዘመን ተሻጋሪ ሙዚቃዎች በፍጹም ሊታሰብ አይችልም። አዲስ ዓመትን ያለ ጥላሁን ገሠሠ “የ13 ወር ፀጋ” እና ያለ አስቴር አወቀ “አበባየሆሽ”፣ ጥምቀትን ያለ ይሁኔ በላይ “ዘገሊላ”፣ ፋሲካን ያለ ታደሰ ዓለሙ “በቀራንዮ ላይ ታየ”፣ ገናን ደግሞ ያለ ፍሬው ኃይሉ “አሲና በል አሲና ገናዬ” ማሰብ እንደማይቻለው ሁሉ፤ የቡሄ በዓልም ያለ አርቲስት ሰለሞን ደነቀ “ስርቅታዬ” ሙዚቃ ሙሉ ሊሆን አይችልም ተብሎ የሚነገርለትና አብዛኛው ሰው የሚስማማበት የዘመን መልክ ነው፤፤

የወለጋ ኪነት ቡድን ካፈራቸው አንጋፋ ድምፃውያን መካከል አንዱ የሆነው ሰለሞን ደነቀ፣ በ1980 ዓ.ም ከቀረበው “አይሆንም እደሪ” የመጀመሪያ አልበሙ ጀምሮ “ሳብዬ” በ1981፣ “ስርቅታዬ” በ1982 እና “ስትለኝ ከርማ” በ1983 የተሰኙ አልበሞችን አቅርቧል።

ከዚህ በተጨማሪም ከኤልሳቤት ተሾመ ጋር “ተው መላዬ’፣ ከእንደልቤ ማንደፍሮ ጋር ደግሞ “በኔ ላይ ሌላ ሰው” የሚሉ ድንቅ ሥራዎችን አበርክቷል።

እንደ “ወላንሳ”፣ “ኩኩሉ” እና “ያ ዳበሌ” ያሉ ዘፈኖቹ ተወዳጅ ቢሆኑም፣ “ስርቅታዬ” ግን በዓሉ በመጣ ቁጥር በትንሽ በትልቁ ዘንድ በቀዳሚነት የሚደመጥ ሥራው ለመሆን በቅቷል።

ከተሠራ ከ36 ዓመታት በኋላም በሕዝብ ልብ ውስጥ ታስቦ የሚኖረው የስርቅታዬ የሥራ ሂደት ከጣዕሙ ባሻገር እጅግ አዝናኝ ገጠመኝ የነበረበት ነው።

አርቲስት ሰለሞን ደነቀ በቅንብሩ ውስጥ የሚደመጠውን የሕፃናት ሆያ ሆዬ ድምፅ በተፈጥሯዊና በትክክለኛው መንገድ ለመቅረፅ በማሰብ በርካታ ሕፃናትን ሰብስቦ ወደ ቀረፃ ስቱዲዮ ይዟቸው አመራ።

ልጆቹ ተረጋግተውና ተዝናንተው ተራቸውን እንዲጠብቁ በማሰብም ድምፃዊ ሰለሞን ደስ የሚል ኬክና ለስላሳ ገዝቶ ሰጣቸው።

ሆኖም ግን ሰለሞን የራሱን የድምፅ ክፍሎች ሠርቶ ጨርሶ ሕፃናቱ የሆያ ሆዬ ድምፅ የሚሰጡበት ክፍል ላይ ሲደርስና ልጆቹን ሊጠራ ሲሄድ ያልጠበቀው ነገር ገጠመው፤ ሕፃናቱ በበሉት ኬክና በጠጡት ለስላሳ ጠግበው በዛላይ ሰለሞን ስለቆየባቸው በከባድ እንቅልፍ ተይዘው ተኝተው ነበር።

ቢቀሰቅሷቸውም ሊነቁ አልቻሉም፤ በመጨረሻም ድምፃዊ ሰለሞን ደነቀ ከድምፃዊት የሺእመቤት ጋር በመሆን የሕፃናቱን ድምፅ በጋራ በመተካት ሥራውን ለማጠናቀቅ ተገደደ።

አንጋፋው አርቲስት ሰለሞን ደነቀ በወቅቱ የገጠመውን ይህን መሰል አዝናኝ አጋጣሚ አልፎ ያበረከተልን ስርቅታዬ፣ ዛሬም ድረስ የቡሄን በዓል በደመቀ ሁኔታ እንድንቀበል መንፈስን የሚያነቃቃ ዘመን ተሻጋሪ ሀብት ሆኖ ቀጥሏል።

ጥበብ እንዲህ በብዙ ውጣ ውረድ አልፋ ነው የትውልድ መታሰቢያ ሆና የምትቀረው።

ተመስገን ኡካሬ
@Arada_Fm

#የኢትዮጵያሙዚቃ #ቡሄ #ሆያሆዬ #ሰለሞንደነቀ #ስርቅታዬ #የቡሄበዓል #ኢትዮጵያ #ባህል #ትዝታ #ጥበብ #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1