በሳውዲ አረቢያ በተፈጸመ ጭካኔ የተሞላበት ግድያ ጋር በተያያዘ አንድ ዋና ተጠርጣሪ በሳውዲ አረቢያ ፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉን የኢትዮጲያ ኤምባሲ አሳወቀ
በሳውዲ አረቢያ በኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ሕገ-ወጥ ድርጊት ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡
በሳውዲ አረቢያ የሚገኙ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳቸው በሚያደርጉት አደገኛ ግጭትና ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ዙሪያ አሳሳቢ መረጃዎች እየወጡ ነው። በጉዳዩ ላይ እርምጃ ለመውሰድም አንድ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር መዋሉ ታውቋል።
ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በሳውዲ አረቢያ የሚገኙ የተወሰኑ ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳቸው ጥቃት ሲፈጽሙ የሚያሳዩ አስደንጋጭ ቪዲዮዎች ሲሰራጩ መቆየታቸው ይታወሳል።
በሳውዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉዳዩን በቅርበት በመከታተል መፍትሄ ለመስጠት ከማህበረሰብ ተወካዮችና ከኮሚቴዎች ጋር በመሆን ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።
ኤምባሲው እንዳሳወቀው፣ እስካሁን በተደረገው ማጣራት ፤ አሳዛኙ ድርጊት የተፈጸመው ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ወደ ሀገሪቱ ገብተው በአል-በሃ እና ገጠራማ አካባቢዎች ተሸሽገው በነበሩ ዜጎች መካከል ነው። ዜጎቹም ባልታወቀ ምክንያት አካባቢን መሠረት ባደረገ ጎሰኛ ክፍፍል እርስ በእርስ ግጭት ውስጥ መግባታቸው ተነግሯል፡፡
ይህንን ሕገ-ወጥ እና አጸያፊ ድርጊት ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረትም አንድ ዋና ተጠርጣሪ በሳውዲ አረቢያ ፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል።
ኤምባሲው ከሀገር ውስጥ ቋሚ አካላት ጋር በመተባበር ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ ጠንካራ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል። በመሆኑም ሕብረተሰቡ ይህንን አጸያፊ ድርጊት ለመግታት በሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት፣ ማንኛውንም ተዓማኒ መረጃ ወይም ጥቆማ ለህግ አስከባሪ አካላት በመስጠት አጋርነቱን እንዲያሳይ ጥሪ ቀርቧል።
Ethio Fm
Source: Yeneta Tube









No comments yet.