ከቆሙ ተሽከርካሪዎች ላይ የሰሌዳ ስርቆት ሲፈፅም የነበረ ተጠርጣሪ እጅ ከፍንጅ ተያዘ፡፡

- Advertisement -
Sidebar AD

ተጠርጣሪ አየነው ፈጠነ የሰሌዳ ስርቆት ድርጊቱን የፈፀመው በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 አትሌቶች መንደር አካባቢ ነው።

በክፍለ ከተማው በተለያዩ ቦታዎች ግለሰቦች ተሽከርካሪዎቻቸውን አቁመው በሚሄዱበት ወቅት እንቅስቃሴዎቻቸውን በመከታተል ሰሌዳዎችን በመፍታት የሳፋሪ ኮም ስልክ ቁጥሩን በወረቀት ፅፎ በመለጠፍ ከአካባቢው በቅርብ ርቀት በመሆን ሲደወልለት ገንዘብ መክፈል እንዳለባቸው ካልከፈሉ ወንጀል እንደሚፈፅምበት እያስፈራራ ከ5ሺህ ብር እስከ 7ሺህ ብር እየተቀበለ እንደሆነ የግል ተበዳዮች በጎሮ አካባቢ ፖሊስ መምሪያ ቀርበው ባመለከቱት መሰረት በምርመራ ክፍሉ ክትትል መጀመሩ ተገልጿል።

በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ የጎሮ አካባቢ ፖሊስ መምሪያ በግልፅ እና በስውር ክትትል በማድረግ ተጠርጣሪው ግለሰብ እንደለመደው የሰዎችን እንቅስቃሴ በመከታተል መንገድ ዳር እና የመኖሪያ ቤት በር አካባቢ የቆሙ ተሽከርካሪዎችን ሰሌዳ በመፍታት ላይ ሳለ እጅ ከፍንጅ ሊያዝም ችሏል፡፡

ፖሊስ በተጠርጣሪው ላይ ባደረገው የምርመራ ማስፋት ተግባር እና በመኖሪያ ቤቱ ባደረገው ፍተሻ ተጨማሪ ሰሌዳዎችን በማግኘቱ የምርመራ መዝገቡን በማደራጀት ክስ ተመስርቶበት በማረሚያ ቤት ሆኖ ጉዳዩን እየተከታተለ ይገኛል።

ህብረተሰቡ በተመሳሳይ ሁኔታ ሰሌዳ እየፈቱ ስልክ እያስቀመጡ የወንጀል ተግባር እየፈፀሙ ያሉ ግለሰቦች በመኖራቸው ጥንቃቄ በማድረግ የፓርኪንግ ጥበቃ ባለበት በማቆም እንዲሁም ድርጊቱ ተፈፅሞ ሲገኝ ለአቅራቢያቸው ፖሊስ መምሪያ ጥቆማ በመስጠት የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ሊተባበሩ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በመልዕክቱ አሳስቧል።

Addis Ababa police



Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1