ዕዳ ቁጭትና እውነት

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | ቴአትር ቤቶች በሚጨናነቁበት በዚያ ሰሞን አንድ እለት ብሩክ ግቢ ውስጥ ሆኖ ወደ ውጭ ሲመለከት በአጥር አጮልቀው፣ ተንጠላጥለው ወይም ተንጠራርተው ወደ ውስጥ የሚመለከቱ ሰዎችን ይመለከታል፡፡ ከእነዚህ ሰዎች አንዷ ልታዋራው እንደፈለገች አይነውሃዋን አይቶ የተረዳው ብሩክ ጠጋ ይላል
‹‹ደህና ነሽ! እዚህ ምን ትሰሪያለሽ?››
‹‹ሥራ ፍለጋ መጥቼ ነው ጋሼ!››
‹‹ነይስኪ በበሩ ዙሪና ግቢ፡፡ ሰሞኑን ለትኬት ቆራጭ መደብ ማስታወቂያ እንደወጣ አውቃለሁ፤ ነይ ግቢ እስኪ በበር ዙረሽ›› ይላታል፡፡
ይህች ሰው በተፈቀደላት መሰረት በበር ገብታ ብሩክን ታገኘዋለች፡፡ ወደ መዝናኛ ክበብ ወስዷት ጭውውታቸውን ይቀጥላሉ፡፡
‹‹እና የትኬት ቆራጭነት መደብ ይሆንሻል?››
‹‹እንደ እሱ አይደለም ጋሼ››
‹‹ሥራ ፈላጊ ነኝ አላልሽም እንዴ?››
‹‹አዎ ሥራ እፈልጋለሁ፤ ግን ድምጻዊ መሆን ነው የምፈልገው››
‹‹እውነት?››
‹‹እውነቴን ነው፤ ጥሩ ድምጽ አለኝ፤ አገሬ እያለሁም እዘፍን ነበር››
‹‹የት ነው ሀገርሽ?››
‹‹የሀረር ልጅ ነኝ››
‹‹ስምሽን ማን ልበል?››
‹‹ሀመልማል – ሀመልማል አባተ››
‹‹በጣም ጥሩ ነዋ፡፡ እስኪ ነገ በጠዋት ነይና በመሳሪያ አጅቤ ድምጽሽን እሞክረዋለሁ፡፡ እና እንደሚሆን እናደርጋለን፤ ለማንኛውም ነገ በጠዋት ነይ›› ብሎ ያሰናብታታል፡፡

ብሩክ በነጋታው ወደ ብሔራዊ ቴአትር ሲያቀና ሀመልማል ገና በማለዳ ደርሳ ኖሮ በር ላይ ቁጭ ብላ ያገኛታል፡፡ ጥበቃው እንዲያስገባት ነግሮ ይዟት ወደ መለማመጃ ክፍል ይሄዳሉ፡፡ በኪቦርድ አጅቧት እንድትዘፍን ያደርጋል፡፡ ጥሩ ድምጽ እንዳላት ተረዳ፡፡

( ከሚለው አዲሱ መጽሐፍ የተወሰደ፡፡ በጃዕፈር መጻሕፍት (ለገሀር) እና በጦቢያ መጻሕፍት (ካዛንችስ) ያገኙታል)


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1