#Ethiopia | የሰው ልጅ በትዳር ውስጥ የሚያልፍበትን ልጅ የማጣት ፈተና እና የሰውን ልጅ ደግነትና ስግብግብነት በስሜት አነቃቂ መልኩ የሚያቀርበው “የደመና ዳንኪረኞች” ቲያትር፣ ከእረፍት በኋላ በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ዘወትር ሐሙስ በ11፡30 ሰዓት ለተመልካች እየቀረበ ይገኛል።
በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት የቲያትር ክፍል ሀላፊ እና የ”ደመና ዳንኪረኞች” አዘጋጅ የሆኑት አለምፀሐይ እጅጉ፣ የሰውን ልጅ ደግነት፣ ስግብግብነትና ራስ ወዳድነት እንዲሁም እናት ለልጇ ያላትን ጥልቅ ፍቅርና ልጅ የማጣትን ፈተና የሚዳስሰው የ “ደመና ዳንኪረኞች” የተሰኘው ቲያትር በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ለመድረክ መብቃቱን ገለጹ።
ቲያትሩ በደራሲ ውድነህ ክፍሌ የተጻፈ ሲሆን፣ የሰው ልጅ በትዳር ህይወቱ ውስጥ የሚያልፍበትን የልጅ ማጣት ውጣ ውረድና ልጅ ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት በትኩረት ያሳያል።
ህሊና ሲሳይ፣ እሰጢፋኖሰ ከበደ፣ መርዐድ ነጋሽ፣ ፋሀድ መሀመድ እና ፅናት አበራ የሚተውኑበት እና ፉአድ መሀመድ ረዳት አዘጋጅነት የቀረበው የደመና ዳንኪረኞች ቲያትር፣ ከዚህ ቀደም በአዲሱ የፍላሚንጎ ቲያትር ቤት ታይቶ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ወደ ሀገር ፍቅር ተመልሶ ዘወትር ሐሙስ በ11 ሰዓት ተኩል ለተመልካች እየቀረበ ይገኛል።
አዘጋጇ አክለው እንደገለጹት፣ በኮቪድ እና በኮሪደር ስራ ምክንያቶች ዝግ የነበሩ የቲያትር መድረኮች አሁን ላይ ትልቅ የመነቃቃት መንፈስ እያሳዩ ሲሆን፣ ማህበረሰብን በመቅረጽ በኩል ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው የቴሌቪዥን ጣቢያዎችና ሚዲያዎችም የማስታወቂያ ክፍያዎችን በመቀነስ የቲያትር ጥበብ ለህዝብ እንዲዳረስ አብረው ሊሰሩ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
በአሁኑ ወቅት የሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት የትኬት አቆራረጥ ዲጂታል በማድረግ ለተመልካች እያቀረበ ሲሆን፣ ከ የ”ደመና ዳንኪረኞች” በተጨማሪ እንደ “ሴዴታ”፣ “የመጨረሻው ፍርድ” እና “አሉ” ያሉ የተለያዩ ቲያትሮችን በማቅረብ ላይ ይገኛል።
አለምፀሐይ እጅጉ ቲያትር ለአእምሮ ትልቅ ምግብ መሆኑን በመጥቀስ፣ ተመልካቾች ወደ ሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት በመምጣት የተለፋበትን የጥበብ ውጤት እንዲታደሙ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በጌትነት ተመስገን
📷 ከበደ መክብብ
#EthiopianTheatre #HagerFikirTheatre #YedemenaDankirenyoch
#EthiopianArts #AddisAbabaEvents
#TheatreInAddis #EthiopianCulture #AfricanTheatre #EthiopianTheatre ##Ethiopia #AddisAbaba



Source: GetuTemesgen









No comments yet.