የሶላር ኃይል አቅርቦት ባላቸው አካባቢዎች ለአዲስ የመኖሪያ ቤት ደንበኞች ነፃ የኤሌክትሪክ ቆጣሪ አገልግሎት ተጀመረ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከዋናው የኤሌክትሪክ ግሪድ ርቀው በሚገኙና በፀሃይ ኃይል (ሶላር) አማራጭ የኤሌክትሪክ አቅርቦት በተሰጣቸው አካባቢዎች ለሚገኙ አዲስ የመኖሪያ ቤት ደንበኞች ነፃ የኤሌክትሪክ ቆጣሪ እንዲገጠም አዲስ አሠራር ጀምሯል።

አዲሱ አሠራር በተለይም ከዋናው የኤሌክትሪክ ግሪድ ርቀው በሚገኙ የገጠር አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች የኤሌክትሪክ አገልግሎትን በቀላሉ እንዲያገኙ እና የኢኮኖሚ አቅማቸው የኤሌክትሪክ ተጠቃሚነታቸውን እንዳይገድብ ለማድረግ የተወሰደ እርምጃ ነው።

አሠራሩ በቅርቡ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ፣ ከሰኔ 2018 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ባሉት ሁለት ሳምንታት ብቻ 3 ሺህ 364 ደንበኞች በኦፍ-ግሪድ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ነፃ ቆጣሪ እንዲጠቀሙ ተደርጓል።

በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ ከዋናው ግሪድ ርቀው የሚገኙ 26 የገጠር ቀበሌዎችና ከተሞች በሶላር ኃይል አማራጭ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተገበረው አዲሱ አሠራር በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች በኢኮኖሚ አቅማቸው ምክንያት ከኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዳይርቁ ለማድረግና ንጹህ ኃይልን በማስፋፋት የኑሮ ደረጃን ለማሻሻል የሚያግዝ ነው።

በሌላ በኩል አገልግሎቱ ከዋናው የኤሌክትሪክ ግሪድ ርቀው የሚገኙ የገጠር ከተሞችንና ማኅበረሰቦችን በሶላር ኃይል የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ባከናወነው የእስካሁን ሥራ፤ 54 የሶላር ኃይል ማመንጫዎችን በመገንባት ከ11 ሺህ በላይ አባወራዎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።

የሶላር ኃይል ማመንጫዎቹ የአካባቢው ማኅበረሰብ ንብረት በመሆናቸው፣ ነዋሪዎች ማመንጫዎቹና መሰረተ ልማቶችን በአግባቡ እንዲጠብቁና እንዲንከባከቡ እንዲሁም የተጠቀሙትን የኤሌክትሪክ ፍጆታ ሂሳብ በወቅቱ እንዲከፍሉ አገልግሎቱ ጥሪ ያቀርባል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ የዜጎችን በአንድ ጊዜ የመክፈል አቅም ችግር ለመቅረፍ ከዋናው የኤሌክትሪክ መረብ ጋር ለተገናኙ ደንበኞች ቆጣሪ በረጅም ጊዜ የክፍያ አማራጭና ከወለድ ነፃ በሆነ መንገድ እንዲያገኙ አገልግሎቱ ማመቻቸቱን ይታወሳል።

#የኢትዮጵያኤሌክትሪክአገልግሎት





Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: