#Ethiopia | በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ ማበልጸጊያ ተቋም አዘጋጅነት ከስድስት ዓመታት በፊት በተካሄደ ጉባኤ ላይ የአማርኛ ቋንቋ ዕድገትና ታሪካዊ አመጣጥን በተመለከተ ሰፊ ውይይት ተደርጎ ነበር።
በወቅቱ በቀረቡ ጥናቶች እንደተመላከተው አማርኛ የሀገሪቱን ብዝኃነት ማስተሳሰር የቻለና በሥነ ልሳን እንዲሁም በሥነ ጽሑፍ ረገድ የዳበረ ታሪካዊ ዕድል ያገኘ ቋንቋ ነው።
ቋንቋው ከግዕዝ የተወረሰ ሀብት ያለው፣ የራሱ ፊደል፣ ቁጥርና ሥርዓተ ነጥብ የተላበሰ ከመሆኑም በላይ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል በአፍ መፍቻነትና በሁለተኛ ቋንቋነት ይነገራል። ግልጽ የቋንቋ ፖሊሲ በመጣጣቱ ምክንያት የብሔራዊ ቋንቋነት ደረጃ ባያገኝም የፌደራል መንግሥቱና የብዙ ክልሎች የሥራ ቋንቋ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል።
አማርኛ ለዚህ ደረጃ ሊበቃ የቻለው በዛጉዌና በሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥታት ዘመን የቤተ መንግሥት ቋንቋ በመሆኑ እንደሆነ ይነገራል።
ሆኖም በዓፄ ይስሐቅና በዓፄ ዓምደጽዮን ዘመን የጽሑፍ ቋንቋ ከመሆኑ በፊት፣ ከቤተ መንግሥት ይልቅ የሠራዊቱና የሕዝቡ መግባቢያ ነበረ። በመሆኑም የቋንቋው ዋና መሠረት ሕዝብና ሠራዊት እንጂ ቤተ መንግሥት እንዳልነበረ ምሁራን ያረጋግጣሉ።
ይህ የሕዝብና የሠራዊት ቋንቋ መሆኑም በሀገሪቱ በሙሉ በስፋት እንዲሰራጭ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።
አማርኛ መላው ኢትዮጵያን የሚያገለግል ብቻ ሳይሆን የበርካታ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን ሰዋስዋዊ ባሕርያት አጣጥፎ የያዘ ልዩ ቋንቋ ነው።
ሆኖም በቅርብ ዓመታት ለቋንቋው የተሰጠው ትኩረት በመቀነሱ፣ ለምሳሌ በ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና አለመካተቱና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትኩረት ማጣቱ በሀገራዊ መግባቢያነቱ ላይ ሥጋት ፈጥሯል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልሳን መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ባየ ይማም እንዳሉት፣ በፌደራል ሥርዓቱ ክልሎች የየራሳቸውን ቋንቋ ለማበልጸግ ሲሰሩ አማርኛ ግን የፌደራል የሥራ ቋንቋ በመሆኑ ብቻ ልዩ ተቋም አዘጋጅቶ የሚያበለጽገው አካል አላገኘም።
አክለውም የትምህርት ፖሊሲው በማንኛውም ቋንቋ መማርን የማይከለክል ቢሆንም፣ ለአንድ ቋንቋ የተወሰነ የአካባቢ ወሰን መስጠት በአፈጻጸም ላይ ክፍተት ፈጥሯል ብለዋል።
ሆኖም ህዝቡ ለአማርኛ ያለው በጎ አመለካከትና ልጆቹን የማስተማር ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ ቋንቋው አዲስ የትንሣኤ ዘመን ላይ ይገኛል።
ሕዝቡ ሀገራዊ መግባቢያ ቋንቋ እንደሚያስፈልግ የሚያምን ሲሆን፣ አማርኛም በጽሑፍና በተደራሽነቱ በኩል ያለውን አቅም ተጠቅሞ ይህንን ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ድረስ የቋንቋ ፖሊሲ የላትም። የቋንቋ ፖሊሲ መኖር በሀገሪቱ ያሉ ሁሉም ቋንቋዎች እኩል የሚያድጉበትና የሚጠበቁበትን ዕድል ይፈጥራል።
በከተሜነት፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪና በብዙኃን መገናኛዎች ታግዞ እዚህ የደረሰው አማርኛ፣ ወደፊት የሚወጣ የቋንቋ ፖሊሲ የሥራና የብሔራዊ ቋንቋ ውዝግቦችን ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል።
ንጉሥ ወዳጅነው
#amhariclanguage #linguistics #ethiopianlanguages #education #languagepolicy #ethiopia #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa
Source: GetuTemesgen








No comments yet.