ተጠርጣሪዎቹ ሰለሞን ቢራራ እሱባለው አግማሴ እና ሳንቾ ጌታቸው የተባሉ ሲሆን የወንጀል ድርጊቱን የፈፀሙት ነሐሴ 3 ቀን 2018 ዓ/ም በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 9 ሌማት ሆቴል አካባቢ ከቀኑ 9፡00 ሠዓት ነው። ግለሰቦቹ በተጠቀሰው አካባቢ ከሚገኝ የግል ተበዳይ መኖሪያ ቤት በመሄድ የአለቃችንን ልጅ ባህር ማዶ ልከህ 5 መቶ ሺ ብር ተቀብለሃል በወንጀል ትፈለጋለህ በማለት ሀሰተኛ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት እና የመከላከያ መታወቂያ በማሳየት ጦር ኃይሎች አለቃችን ጋር እንወስድሀለን በማለት በተሽከርካሪ አግተውት ጉዞ ይጀምራሉ።
ተጠርጣሪዎቹ የተወሰነ ርቀት እንደተጓዙ የተሽከርካሪያቸውን መሪ አዙረው ወደ ቢሾፍቱ በማድረግ ከፈጣን መንገዱ እንደደረሱ ከአለቃችን ጋር ካደረስንህ ከባድ ቅጣት እና ተጠያቂነት የሚጠብቅህ በመሆኑ በሞባይል ባንኪንግ ብር አስገባልን እና እንልቀቅህ ይሉታል።
የግል ተበዳይ የሰራሁት ወንጀል የለም ወደ ህግ ውሰዱኝ በማለቱ ደብድበው 6 መቶ ሺ ብር በሞባይል ባንኪንግ በማስላክ ከተሽከርካሪ አውርደው ጥለውት መሰወራቸውን በየካ ክ/ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ የላም በረት አካባቢ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ኢዮብ ተከተል ገልፀዋል፡፡
ፖሊስ ባደረገው ክትትልም ም/መቶ አለቃ ሰለሞን ቢራራ የተባለን ተከሳሽ የቢሾፍቱ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ባደረገው ትብብር በቁጥጥር ስር በማዋል በተከናወነው ምርመራ የማስፋት ተግባር ከመከላከያ ሰራዊት የከዳ ም/መቶ አለቃ እሱባለው አግማሴ የተባለን ደግሞ ግለሰብ ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በቁጥጥር አውሎታል።
ፖሊስ የምርመራ እና የክትትል ስራውን በመቀጠልም ገንዘብ አላቸው የሚባሉ ሰዎችን መረጃ በማጣራት ለወንጀል ፈጻሚዎች ጥቆማ የሚሰጥን ተጠርጣሪ ሳንቾ ጌታቸው የተባለን ግለሰብ ላምበረት መናኸሪያ አካባቢ በቁጥጥር ስር ሊያውለው መቻሉን የምርመራ መዝገቡ ያስረዳል፡፡
ከተወሰደው ገንዘብ 135 ሺ ብር እንዲሁም በዚሁ ብር የተገዛ 70,000 ሺ ብር የሚገመት ላፕቶፕ በኤግዚቢትነት በመያዝ ቀሪውን ብር ለማስመለስ እና ያልተያዘ አንድ ተጠርጣሪን ለመያዝ ምርመራው እና የክትትል ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን አዛዡ አመላክተዋል።
ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለከተሞች አምስት ተመሳሳይ የእገታ ወንጀሎችን መፈጸማቸውን ለመርማሪ ፖሊስ ቃላቸውን የሰጡ ሲሆን በዚህም ጉዳይ ከሌሎች ክፍለ ከተሞች ጋር ጭምር በመነጋገር በጥልቀት እየተሰራበት መሆኑን አዛዡ ጠቁመዋል።
ህብረተሰቡ የጸጥታ አካል ነን ወንጀል ስለፈጸማችሁ በህግ ትፈለጋላችሁ፣ ወደ ህግ ቦታ ነው የምንወስዳችሁ በሚሉ ቃላት በመጠቀም አታለው ወንጀል የሚፈጽሙ አካላት መኖራቸውን አውቆ እንደዚህ አይነት አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙ በፍጥነት በአቅራቢያው ላለ የጸጥታ ተቋም ማሳወቅ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ መልዕክቱን አስተላልፏል።
Addis Ababa police

Source: Yeneta Tube









No comments yet.