#FastMereja I በ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና ከተፈተኑ ተማሪዎች መካከል 12.8 በመቶ ወይም 70,544 የሚሆኑት 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ በማምጣት ማለፋቸውን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዛሬው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳብራሩት፣ በዘንድሮው የፈተና ዘመን ለተፈጥሮ እና ማህበራዊ ሳይንስ ፈተና ከተመዘገቡ 563,960 ተማሪዎች ውስጥ 550,210 ተማሪዎች ፈተናውን ወስደዋል። ባለፈው ዓመት ከተመዘገበው የ8.9 በመቶ የማለፍ ምጣኔ ጋር ሲነጻጸር የዘንድሮው ውጤት የ20 ሺህ ያህል ተማሪዎች ብልጫ እንዳለው ተገልጿል።
እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፣ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ከ50 በመቶ በላይ ያመጡ ተማሪዎች ስብጥር በተፈጥሮ ሳይንስ 16.58 በመቶ እንዲሁም በማህበራዊ ሳይንስ 8.33 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል።
ከ ከፍተኛው ውጤት አንጻር፣ በተፈጥሮ ሳይንስ ከ600 ነጥብ ከፍተኛው ውጤት በወንድ 591.64፣ በሴት ደግሞ 583.03 ሆኖ ተመዝግቧል። በማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ደግሞ በወንድ 576.25 እንዲሁም በሴት 569.17 ከፍተኛው ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል።
በሌላ በኩል ተማሪዎችን ካስፈተኑ የሀገሪቱ ትምህርት ቤቶች መካከል 88 ትምህርት ቤቶች 100 በመቶ ተማሪዎቻቸውን ያሳለፉ ሲሆን፣ 565 ትምህርት ቤቶች ደግሞ አንድም ተማሪ ማሳለፍ አልቻሉም። ይህም ባለፈው ዓመት አንድም ተማሪ ካላሳለፉ 1,232 ትምህርት ቤቶች ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሻሻል ማሳየቱን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
በትምህርት ዘርፉ እየተተገበሩ ያሉ የሪፎርም እርምጃዎች ለውጤቱ መሻሻል አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ተገልጿል።
Source: FastMereja









No comments yet.