🇮🇹
ተስፋዬ እሸቱ(ረዳት ፕሮፌሰር)
#Ethiopia | ፍሎረንስን ስጎበኝ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ግን ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ጎብኚ ፍሎረንስ ሁሌም አዲስ ናት፤ ፍሎረንስን አንድ ጊዜ አይቶ፣ “አይቼ ጨርሻለሁ” ማለት ዘበት ነው። በተመለስክ ቁጥር አዲስ ታሪክ የምትነግርህ ከተማ ናት። የሰው ልጅን የፈጠራ ምትሃት የምትገልጥልህ ከተማ ሳትሆን፣ እሷ ራሷ የሆነች መንፈስ ነገር ናት። ፍሎረንስ ከሚሏት “ውቢት” ቢሏት የተሻለ ነበር።
የህዳሴው (Renaissance) መፍለቂያ ተደርጋ በምትታወቀው በዚህች ከተማ፣ ታሪክ በሕንፃዎቿ፣ በአደባባዮቿ፣ በቅርጻ ቅርጾቿና በጎዳናዎቿ ላይ ሲንቀሳቀስ ታያለህ። “በፍሎረንስ መራመድ፣ በታሪክ ውስጥ መራመድ ነው” ይላሉ፤ እውነት አላቸው።
ታዲያ ጉዞዬን ከታላቁ Santa Maria del Fiore (Duomo) ካቴድራል ጀመርኩ። ከዚያም ወደ Piazza della Signoria ተጓዝኩ፤ Palazzo Vecchioንና በአደባባዩ የሚገኙትን ድንቅ ቅርጻ ቅርጾች ተመለከትኩ። ተመለከትኩ ብቻም አይደለም፤ ለሰው ልጅ ረቂቅ የፈጠራ ጥበብ እጅ ነሳሁ።
ቀጥዬም ወደ Galleria dell’Accademia di Firenze አቀናሁ።
ወደዚህ ስፍራ የመጣሁት የMichelangelo ድንቅና ገራሚ የቅርጽ ሥራ የሆነውን ዳዊትን (David) በዓይኔ ለማየት ነበር።
ዳዊትን በዓይኔ ሳየው የተሰማኝን ስሜት በቃላት መግለጽ ይከብደኛል።
ይህ ከነጭ እብነ በረድ የተቀረጸ ግዙፍ ሥራ በMichelangelo ከ1501 እስከ 1504 የተሠራ ሲሆን፣ ቁመቱ 5.17 ሜትር፣ ክብደቱም ወደ 5.5 ቶን ይደርሳል። በ1504 በPiazza della Signoria፣ Palazzo Vecchio አጠገብ እንዲቆም ተደርጎ፣ ቀስ በቀስም የፍሎረንስ ነፃነትና የሪፐብሊካዊ ጥንካሬ ምልክት ሆነ። በ1873 ደግሞ ወደ Galleria dell’Accademia ተዛወረ። (ከተሳሳትኩ እታረማለሁ)
ዳዊትን ከፊቱ ቆሜ ሳየው በድጋሚ ማመን አልቻልኩም። እንደ ተራ ጎብኚ ግን በተለየ ሁኔታ የሳቡኝ ነገሮች አሉ።
ፊቱና ዓይኖቹ፦ የቅርጹ አቀራረብ ዳዊት ጎልያድን ከመጋፈጡ በፊት ያለውን የውጥረት ቅጽበት የወከለ ይመስላል። በመጽሐፍ ቅዱስ የምናውቀው የድል ታሪክ ከመፈጸሙ በፊት ያለው ጸጥታ ተመርጦ በየዓይኖቹ ትኩረት፣ በቅንድቦቹ መኮሳተር ተገልጾል። ከፊቱ ቆመህ ስታየው የዳዊትን ውጥረት አንተም ትጋራዋለህ።
ቀኝ እጁ፦ ከሰውነቱ አንፃር ትንሽ ግዙፍ ሆኖ ይታያል። የደም ሥሮቹ፣ ጅማቶቹ፣ የጣቶቹና የእጅ መገጣጠሚያዎቹ በእንዲህ ያለ ዝርዝር ስለተቀረጹ፣ በደም ሥሮቹ ውስጥ ደም እየተዘዋወረ ያለ እስኪመስል ድረስ ሕያው ይመስላል።
ወንጭፉ፦ ዳዊት ጎልያድን የሚጋፈጥበት መሣሪያ ቢሆንም፣ Michelangelo ግን ጎልቶ እንዲታይ አላደረገውም። በትከሻውና በጀርባው በኩል በጥንቃቄ ካላስተዋልክ ሊታይህ አይችልም። ለእኔ ይህ አቀራረብ ዳዊት ምን ያህል በእግዜሩ እንደተማመነ የሚያሳይ መሰለኝ።
አቋቋሙ፦ የሰውነቱ ክብደት በአንድ እግሩ ላይ አርፎ፣ ሌላኛው እግር ዘና ብሎ ይታያል። በዚህ አቋቋምም ዳሌው፣ ደረቱና ትከሻው በተለያየ አቅጣጫ ዘንበል ያሉ በመሆናቸው፣ ድንጋዩ ተንቀሳቃሽ ሕያው ሰው ይመስላል።
ከቀኝ እግሩ ጀርባ ያለው የዛፍ ግንድ እንኳ ተራ ጌጥ አይደለም። ግዙፉን የእብነ በረድ ቅርጽ በመደገፍ መዋቅራዊ ጥንካሬ ይሰጠዋል፤ እንደ ተፈጥሯዊ አካልም ከቅርጹ ጋር ተዋህዷል።
ምን ልበላችሁ፤ ዳዊትን በፎቶ ማየትና ከፊቱ ቆሞ ማየት ፈጽሞ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው።
ከ500 ዓመታት በፊት የሰው ልጅ ከእብነ በረድ ላይ ሕይወትን በዚህ ልክ መቅረጽ መቻሉ፣ የሰው ልጅ የፈጠራ አቅምና የጥበብ ረቂቅነት ምን ያህል ከፍ ያለ ደረጃ እንደነበረው የሚያሳይ ነው።
እኔ የምለው ግን፣ ዘመን ቁጥሩ ሲጨምር የሰው ልጅ ጥበብ እያደገ ነው ወይስ እየኮሰሰ ነው የመጣው?!…
ሰላም ዋሉ! 🇮🇹
#Florence #Italy #Renaissance #MichelangeloDavid #ArtAndHistory #TravelNotes #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa


Source: GetuTemesgen









No comments yet.