#Ethiopia | ከነሐሴ 10 ቀን ጀምሮ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም በደመቀ ሁኔታ ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች የቮሊቦል ሻምፒዮና በዛሬው እለት ፍጻሜውን አግኝቷል።
ስድስት የክልል ክለቦች ዋንጫውን ለማንሳት ባደረጉት ብርቱ ፍልሚያ፣ የአርሲ ክለብ የ2018 ዓ.ም ውድድር አሸናፊ ለመሆን ችሏል። በፍጻሜው ጨዋታ አርሲ ከተማ አዴት ከተማን 3 ለ 1 በሆነ ውጤት በመርታት ነው የሻምፒዮንነት ዘውዱን የተቀዳጀው።
በዚህም መሰረት ውድድሩን ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁት አርሲ፣ አዴት ከተማ እና ስኬት ባንክ ያሳዩትን ድንቅ ብቃት ተከትሎ ወደ 2019 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።
በመዝጊያ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ስሜነህ በሴ (ዶ/ር)፤ ለአሸናፊዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት ካስተላለፉ በኋላ የስፖርቱን የወደፊት ጉዞ አስመልከተው ጠንከር ያለ ሃሳብ አንስተዋል። ፕሬዚዳንቱ እንደገለጹት የክለቦች በየጊዜው መፍረስ ለቮሊቦል ስፖርት እድገት ዋነኛ ማነቆ እና ፈተና በመሆኑ ይህ ችግር ሊቀረፍ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ይህንኑ ችግር ለመቅረፍ እና ክለቦች ቀጣይነታቸውን ጠብቀው እንዲዘልቁ ለማስቻል ፌዴሬሽኑ የፋይናንስና የትጥቅ ድጋፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ዶክተር ስሜነህ አበክረው ገልጸዋል። አክለውም የተለያዩ ተቋማት ለስፖርቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎች በትኩረት እንደሚሰሩ በመጠቆም፣ የቮሊቦል ስፖርት በሀገሪቱ ተገቢውን ስፍራ እንዲያገኝ ጥሪ አቅርበዋል።
ጌትነት ተመስገን
📷 ከበደ መክብብ
#EthiopianVolleyball #ጌጡ #Getu
#EthiopianVolleyballFederation
#EthiopianPremierLeague #RefereeTraining
#EthiopianSports #VolleyballEthiopia



Source: GetuTemesgen








No comments yet.