የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት በሀገራችን ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ፣ እንደ ሌላ “አድዋ” ሊቆጠር የሚችል ታላቅ ሀገራዊ ስኬት ነው። ለአምስት ዓመታት ያህል ገደማ ከፍተኛ ጥረት ሲደረግበት የቆየው፣ ከታች ከማህበረሰቡ መገኛ ጀምሮ ወደ ላይ አጀንዳዎችን ያሰባሰበው ይህ ሂደት፣ 4,000 ተመካካሪዎችን በማሳተፍ ለ46 ቀናት የፈጀ ጥልቅና ታሪካዊ ውይይት አስተናግዷል። ይህ ሂደት ለትውልዳችን የተከፈተ ልዩ አሻራና የብሩህ ተስፋ መሰረት ነው።
ከዚህ ታላቅ መድረክ የተገኘው ከምንም በላይ የላቀው ድል፣ በአዲስ መልክ የዳበረው የመነጋገርና የመደማመጥ ባህል ነው። ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ውስጥ የማይነገሩ፣ መነጋገር የማይቻልባቸው እና ለማንሳት የሚያሸማቅቁ በርካታ ጉዳዮች በግልጽ ወደ መድረክ መጥተዋል። ተመካካሪዎች በነፃነት ተነጋግረዋል፣ ተከራክረዋል፣ ተጨቃጭቀዋል፤ ነገር ግን አንዱ የሌላውን ህመም በመረዳትና ራስን በሌላው ጫማ ውስጥ በማስገባት፣ ከብዙ ፍጥጫ በኋላ በመቀራረብ ወደ መሃል መምጣት ችለዋል። ይህ እርስ በርስ የመተሳሰብ ባህል የሀገራችን የሰላም ጽኑ መሰረት ነው።
ይህንንም ተከትሎ በመድረኩ ከቀረቡት ከ400 በላይ ምክረ ሀሳቦች ውስጥ፣ 396ቱ ሀገራችንን ወደ ዘላቂ ሰላምና ልማት በሚያመራ መልኩ በታላቅ ስምምነትና በአንድነት መንፈስ የጋራ መግባባት ተደርሶባቸዋል። አንድ አይነት ስምምነት ላይ ያልተደረሰባቸው እና ለቀጣይ ውሳኔ በአማራጭነት የተያዙት አራት ዋና ዋና አጀንዳዎች ብቻ ሲሆኑ፣ እነሱም በሚከተለው መልኩ በዝርዝር ቀርበዋል፦
1ኛ -የመንግስት አወቃቀር ሥርዓት፡- ሀገራችን አሁን እየተከተለችው ባለው የፓርላማ ሥርዓት (Parliamentary System) እንዲቀጥል ከስምምነት ከተደረሰ በኋላ :- መራሄ መንግስቱ በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚለዉ ቀርቶ፣
👉አማራጭ አንድ :-ከፓርላማ የሚመረጥ ፕሬዜዳት ይሁን የሚል እና፣
👉አማራጭ ሁለት:-በህዝብ በቀጥታ የሚመረጥ ፕሬዜዳት ይሁነ የሚሉ 2 አማራጮች የቀረቡበት
2ኛ-የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባልነት ውክልና፡-
👉አማራጭ አንድ:-የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በቀጥታ በሕዝብ ምርጫ የሚወከሉበት አሰራር ይዘርጋ
👉አማራጭ ሁለት:-አሁን ባለው የአወካከል ሥርዓት ይቀጥል የሚሉ 2 አማራጮች የቀረቡበት
3ኛ-የሰንደቅ ዓላማ አርማ፡- በሰንደቅ ዓላማችን አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት ላይ ሙሉ በሙሉ ስምምነት የተደረሰ ሲሆን፤ ልዩነቱ ያለው በመሃል ላይ በሚኖረው አርማ ላይ ነው። በዚህም
👉አማራጭ አንድ :-አሁን ያለው አርማ እንዳለ ይቀጥል
👉አማራጭ ሁለት:-አርማዉ በጥናት ተሻሽሎ ይፅደቅ የሚሉ 2 አማራጮች የቀረቡበት
4ኛ-በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይም ከቀረቡት በርካታ ነጥቦች ውስጥ በአብዛኛዎቹ ላይ ፍጹም መግባባት የተፈጠረ ሲሆን፣በአንድ ጉዳይ ላይ ብቻ አማራጭ ሀሳብ ቀርቧል።
በቅድሚያ ስምምነት የተደረሰባቸዉ ጉዳዮች:-
👉 አዲስ አበባ የፌዴራሉ መንግሥት (የኢትዮዽያ) ርዕሰ ከተማ መሆኗን፤
👉 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራስን በራስ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን እና ነፃነት እንዳላት፣
👉 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌዴራሉ መንግሥት እንደሚሆን፤
👉 የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌዎች መሠረት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚወከሉ
👉 – በህገመንግስቱ በአንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5 ላይ ተጠቅሶ የነበረው የኦሮሚያ ከአዲስ አበባ “ልዩ ጥቅም” ታገኛለች የሚለው ሐረግ አሁን በተደረገዉ ዉይይት ይህ ተቀይሮ “የጋራ ተጠቃሚነት” በሚለዉ እንዲተካ ፣እንዲሁም የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ፣የአፍሪካ ፣ አዲስ አበባ የፌዴራል መንግስቱና የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ መሆኗን ሁሉም ተመካካሪዎች በሙሉ ድምጽ ተስማምተውበታል።
ልዩነት ተፈጥሮ በአማራጭነት የተያዘው አንድ ነጥብ ብቻ ነው። ይኸውም አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማ መሆኗ በፌዴራል ሕገ-መንግስቱ ውስጥ እንዴት ይካተት በሚለው ላይ ነው፦
አማራጭ አንድ፡-አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሃል የምትገኝ፣ በአስተዳደርና በአገልግሎት የተሳሰረች፣በመሆኗ እንዲሁም ላለፋት 35 አመታት የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ አዲስ አበባ ሆና ስላገለገች ይህ በፌዴራል ሕገ-መንግስቱ ላይ በግልጽ ይጠቀስ በአንድ አማራጭ፣
አማራጭ ሁለት :-የኦሮሚያ ከተጠቀሰ የሁሉም ክልል የዋና ከተማ በፌዴራል ሕገ-መንግስቱ ላይ በግልጽ ይጠቀስ (ይካተት) የሚሉ 2 አማራጮች የቀረቡበት ናቸዉ።
ከነእነዚህ ጥቂት በአማራጭነት የተያዙ አጀንዳዎች በማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው የአዲስ አበባን ጉደይ ነጥሎ በተዛባ መልኩ የሀሰት መረጃ በመሰራጨቱ ትክክል አይደለም።
እነዚህ አማራጮች:ከጥቃቅን የቡድን ውይይቶች ጀምሮ 500 ተሳታፊዎች እስከነበሩበት መድረክ ድረስ የተደረጉ ክርክሮች፣ የቃለ-ጉባኤ ጽሑፎች፣ እንዲሁም የድምጽና የምስል መረጃዎች በሙሉተፈትሸዉ የትኛው አማራጭ ለሀገር ዘላቂ ሰላምና አንድነት ይጠቅማል የሚለውን በጥልቀት በመመዘን እና አብዛኛዉ ተወያይ የደገፈዉ አማራጭ ለይቶ የምክክር ኮሚሽኑ በህግ በተሰጠዉ አሰራር መሰረት የመጨረሻውን የውሳኔ ሀሳብ ለመንግስት እንደሚቀርብ ገልጿል።
እውነታው ግን ይህ ነው፦ የምክክር ሂደቱ እና የተሳታፊዎቹ ውይይት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በቃለ ጉባኤ፣ በቪዲዮ እና በምስል በአግባቡ የተሰነደና በታሪክ ማህደር የተቀመጠ ነው።
በአጠቃላይ ሲታይ ኢትዮጵያውያን አሸንፈዋል! ይህ የምክክር ሂደት የተራራቀውን ያቀረበ፣ የጠነከረውን ያለዘበ እና የጋራ መግባባት በሩን ወለል አድርጎ የከፈተ ታሪካዊ የድል ብሥራት ነው። እንዲህ ዓይነት ታላቅ ሀገራዊ መድረክ ተፈጥሮና በርካታ አጀንዳዎች ላይ ከዳር እስከ ዳር ስምምነት ተደርሶ ሳለ፣ “እኔ ካልሰራሁት”፣ “የኔ ፍላጎት ብቻ ካልተሟላ” ወይም «እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል» በሚል ኋላ ቀር እና አፍራሽ አስተሳሰብ በማህበራዊ ሚዲያ የተዛቡ መረጃዎችን በማሰራጨት የምክክሩን ሂደትና የሕዝቡን ስኬት ለማጠልሸት የሚሞክሩ አካላት ድርጊት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና ሊወገዝ የሚገባው ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በእርስ በመደማመጥና በመከባበር ትልቅ ድል አስመዝግቧል። ይህንን የተወሳሰበ ሀገራዊ ሂደት በስኬት እንድናጠናቅቅ፣ በሕዝቦች መካከል የመግባባት መንፈስን ላሰፈነ እና ኢትዮጵያውያንን ለዚህ የድል ምዕራፍ ላበቃ ፈጣሪ አምላክ የላቀ ምስጋና ይገባዋል።
“ገዛህኝ ከምክክር ተሳታፊ”



Source: FastMereja









No comments yet.