አዲስ አበባ፦ የዜጎች ቀይ መስመር!

- Advertisement -
Sidebar AD

——————–
(የግል አስተያየት)

አዲስ አበባ የኢትዮጵያውያን መናገሻ፣ የበርካታ ብሔረሰቦች ባህሎች ለዘመናት ተቀይጠው “ከተሜ” ወይንም “አዲስ አበቤ” የሚባል የተለየ ማንነት መገለጫዋ አድርጋ ያበጀች፣ የአፍሪካ ኅብረት እና የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እንዲሁም በፍጥነት እያደገች ያለች የዓለማችን አንዷ የዲፕሎማሲ የስበት ማዕከል ናት።

ቀደም ሲል፣ ሀገራዊ ምክክሩን ላለመረበሽ ስል ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በመገናኛ ብዙኅን በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ አቋሞቻችውን ማቅረባቸውን በመተቸት፣ አጀንዳው ከሜዳ ወደ ምክክር አዳራሹ እንዲመለስ ጥሪ አቅርቤ ነበር።

አሁን ላይ የምክክሩ ሂደት ከሞላ ጎደል በመጠናቀቁ እና በእንጥልጥል ባሉ የአዲስ አበባ ጉዳዮች ላይ ዜጎች በተለይም የአዲስ አበባ ነዋሪ ግንዛቤ ቢሆን፣ ለኮሚሽኑም ውሳኔ ተጨማሪ ግብአት ቢሆን ብዬ ጥቂት ሃሳብ ልሰንዝር። በምክክሩ መድረክ ያራመድናቸውን አቋሞች እና ቀደም ብዬ በአደባባይ ሳቀርባቸው የቆየኋቸውን እና “ምክንያታዊ የምላቸውን ሙግቶቼን ይዤ እመለሳለሁ” ባልኩት መሠረት ለአንባቢያን ማጋራት ተገቢ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

ሌሎች ምን ይላሉ?

በምክክሩ ላይ አዲስ አበባን “የእኔ ናት የለም የአንተ አይደለችም” የሚለው ንትርክ የተካረረ ሲመጣ አንድ ከደቡብ አካባቢ የመጣ ተመካካሪ “የአዲስ ከበባ ጉዳይ የሁለት ብሔሮች ጉዳይ ብቻ አድርጎ ማየት ስህተት ነው። ከሁለቱ ብሔሮች ውጪ ያለን 75 ብሔሮችንም ይመለከተናል። ለምሳሌ በጋሞ፣ በጎፋ እና በአካባቢው አዲስ አበባ “ቱንጋ” ትባላለች” ያለውን ሳስብ አዲስ አበባ ማንም በብቸኝነት የባለቤትነት ጥያቄ የማያቀርብባት የኢትዮጵያ የዜጎች ቀይ መስመር መሆኗን ይገነዘባል።

በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት በአንድ በኩል በአንቀጽ 49(2) ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች «ሙሉ የራስ-አስተዳደር መብት» ሲሰጥ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአንቀጽ 49(5) የኦሮሚያ ክልል በማኅበራዊ አገልግሎቶች፣ በተፈጥሮ ሀብቶችና በጋራ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ባለው «ልዩ ጥቅም» ዙሪያ ዕውቅና ይሰጣል።

ነገር ግን እነዚህን ሁለቱን ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌዎች ከአውዳቸው ውጪ ለጥጦ በመተርጎም፣ ከ8 ሚሊዮን በላይ የሚገመት ሕዝብ የሚኖርባትን ሜትሮፖሊታን ከተማ “የአንድ ክልል ርእሰ ከተማ ትሁንልን” ማለት በሕግም ሆነ በዓለም አቀፍ የፌዴራሊዝም ልምድ ታይቶም ተሰምቶም የሚታወቅ አሠራር አይደለም።

ዓለም አቀፍ ልምዶች

ላለፉት 50 ዓመታት የኦሮሞ ብሔርተኞች አዲስ አበባን ጠቅልሎ በባለቤትነት የመረከብ ፍላጎት አንዱ የትግል ማዕከል መሆኑ ምሥጢር አይደለም። የአደባባይ እውነት ነው። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በአዲስ አበባ ላይ ለሚያቀርበው የ”ይገባኛል” ጥያቄ ምክንያታዊ ለማስመሰል ከሚያነሷቸው አስረጂዎች አንዷ የቤልጂየም ዋና ከተማ ብራስልስን፣ የሳርዬቮን ልምድ ነው። ነገር ግን ብራስልስም ሆነች የሳርዬቮ ሁኔታ ፈጽሞ የኦሮሚያን የይገባኛል ጥያቄ የሚደግፉ አይደሉም። በወፍ በረር እንመልከታቸው፤

ብራስልስ (ቤልጂየም)

ብራስልስ ራሷን የቻለች የዋና ከተማ ክልል (Brussels-Capital Region) ናት። በግዛት ደረጃ የፍላንደርስ (የደች ተናጋሪ) ወይም የዋሎኒያ (የፈረንሳይኛ ተናጋሪ) ክልል አካል አይደለችም። ያም ሆኖ ቤልጂየም የሁለቱንም ማኅበረሰቦች የቋንቋ፣ የትምህርትና የባህል ጥቅሞች ታስከብራለች እንጂ ከተማዋን ለአንድ የብሔር ማንነት የብቸኝነት ባለቤትነት ነጥላ አታስረክብም። የባህልና የቋንቋ ጥቅሞችን ማክበር ማለት ከተማዋን ለአንድ ብሔረሰብ ርእሰ-ከተማነት ነጥሎ መስጠት ማለት አይደለም።

ሳራዬቮ (ቦስኒያ እና ሄርዞጎቪና)

ከተማዋ የቦስኒያ እና ሄርዞጎቪና ሀገራዊ መዲና እንዲሁም የቦስኒያ-ሄርዞጎቪና ፌዴሬሽን አባላት የጋራ ከተማ ሆና ታገለግላለች። ነገር ግን ፌዴሬሽኑ ለአንድ ብሔር ብቻ ተለይቶ የተሰጠ ብሔራዊ ክልል አይደለም። ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱም የበርካታ “መሠረታዊ ብሔሮችን” (Constituent Peoples) ዕውቅና የሚሰጥና የፖለቲካ እኩልነታቸውን የሚያረጋግጥ ነው። ሳርዬቮ በአንድ ብሔረሰብ ባለቤትነት የተያዘች አይደለችም።

አስካሁን ባየኋቸው ጥናቶች የፌደራል መዲናን፣ በአንድ ብሔረሰባዊ ማንነት ዙሪያ ለተደራጀ ክልል በተደራቢነት ዋና ከተማ አድርጎ ለመስጠት የሚያስችል አንድም አሳማኝ ዓለም አቀፍ ተሞክሮም ሆነ ሕጋዊ ማረጋገጫ የለም። (አለ! የሚል ካለ ወዲህ ይበል)

የብሔር ፌዴራሊዝም እና አዲስ አበባ

አዲስ አበባን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ርእሰ ከተማ ማድረግ የክልሉ መንግሥት መሥሪያ ቤቶችን መቀመጫ ከመወሰን ያለፈ ሰፊ ፖለቲካዊና ሕጋዊ አንድምታ አለው። በምክክሩ ወቅትም “መቀመጫ” የሚለው ቃል ይሰረዝልን በሚል የተነሳው ተቃውሞ እና ኮሚሽኑም ፓለቲካዊ ውሳኔ በሚመስል አኳኋን ቃሉን “ሰርዤዋለሁ” ማለቱ የዚሁ የተለጠጠ ፍላጎት ማሳያ ነው።

በኢትዮጵያ የብሔር ፌዴራሊዝም አደረጃጀት ውስጥ ከተማን ለአንድ ክልል “ርዕሰ ከተማ” አድርጎ መስጠት፣ በተዘዋዋሪ የባለቤትነት (Ownership) እና የሥልጣን ወሰን (Jurisdiction) መስጠት መሆኑ ግልጽ ነው። ይህንን ማድረግ ደግሞ ማንነታቸውን እንደ «አዲስ አበቤ» ለሚገልጹ የከተማዋ ነዋሪዎችና ለተደባለቀ ማንነት ባለቤቶች እንዲሁም ራሳቸው በኢትዮጵያዊ ማንነት ለሚገልጹ ዜጎች “ከተማዋ ሁላችንንም በእኩልነትና በዜግነት መብት ታስተናግዳለች? ወይስ አንዳንዶቻችን ባለቤት፣ ሌሎቻችን ደግሞ በእንግድነት የምታኖረን ትሆናለች?” የሚል መሠረታዊ ጥያቄ ያስነሳል።

አዲስ አበባ እና ኦሮሚያ

አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የምትገኝ እንደመሆኗ መጠን፣ ሁለቱ አካላት በተፈጥሮ አቀማመጣቸው ተቀራራቢና የሚተጋገዙ እንጂ ጠበኞች እና ተፎካካሪ ሊሆኑ አይገባም። የከተማዋ መለጠጥ፣ የውኃ አቅርቦት፣ የቆሻሻ አወጋገድ፣ የትራንስፖርት ትስስር፣ የአካባቢ ጥበቃና የፀጥታ ጉዳዮች የጋራ የሜትሮፖሊታን አስተዳደር (Metropolitan Governance Framework) ወይም የጋራ የታስክ ፎርስ አደራጅቶ በትብብር መስራትን ይጠይቃሉ።

ነገር ግን ይህ ተግባራዊና ኢኮኖሚያዊ ትብብር (Functional Cooperation) በምንም ዓይነት መልኩ አዲስ አበባን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት «ርዕሰ መዲና» ወደ ማድረግ የፖለቲካ ውሳኔ ማምራት የለበትም።

ከተማዋን የክልሉ መዲና ማድረግ የክልሉን ሕገ-መንግሥታዊና አስተዳደራዊ ሥልጣን በከተማዋ ላይ በፖለቲካዊ መልኩ የመጫን ሥጋት አለው፣ ትብብሩን በጋራ ጥቅም ላይ በተመሠረተ የቴክኒክና የኢኮኖሚ ማህቀፍ ብቻ መወሰን አስፈላጊ ነው። ለዚህም ነው አዲስ አበባ በፖለቲካ ጫና ወይም አላስፈላጊ ውጥረት በማንገስ ለአንድ ወገን ባለቤትነት ተላልፋ መሰጠት የማትችል የዜጎች ቀይ መስመር ናት የምለው!

ሰላም

————-
እናንተስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ትላላችሁ?
በጨዋነት ተወያዩበት።


Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: