#Fastmereja:-በኢትዮጵያ በሴሬብራል ፓልሲ (CP) ምክንያት ተደራራቢ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ህፃናት እና ወላጆቻቸውን በመደገፍ ላይ የሚገኘው «እዝነት አካል ጉዳተኛ ህፃናትና ወላጆች መርጃ ድርጅት» ለ3ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም የሴሬብራል ፓልሲ ቀን አስመልክቶ ታላቅ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ እና የህዝብ እግር ጉዞ ማዘጋጀቱን አስታወቀ።
ድርጅቱ በዛሬው ዕለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከተው፣ «ለሲፒ ጉዳተኛ የነገ ተስፋ እጓዛለሁ» በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ይህ ታላቅ የእግር ጉዞ በመጪው ጥቅምት 8 ቀን 2019 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2:00 ሰዓት ጀምሮ ከፒያሳ አድዋ ዐዐ እስከ ኩባ ፓርክ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
የድርጅቱ መስራች እና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ዘቢባ አህመድ በመግለጫቸው እንደተናገሩት፣ በሴሬብራል ፓልሲ ምክንያት ተደራራቢ ጉዳት የደረሰባቸው ህፃናት ያለ ሰውና መሳሪያ ድጋፍ መቆም፣ መቀመጥና መራመድ የማይችሉ እንዲሁም ስሜታቸውን ከማልቀስ ውጭ መግለጽ የማይችሉ መሆናቸዉን ገልፀዋል።
ወ/ሮ ዘቢባ አክለዉም በርካታ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦችም በድህነት ምክንያት ህፃናቱን ከፀሐይና ከሰው እይታ ሰውረው በቤት ውስጥ ለማቆየት መገደዳቸውን ገልጸዋል።
በዕለቱ የሪባን መቁረጥ ሥነ-ሥርዓት፣ የማርሽ ባንድ፣ የማስኮት (Mascot) ትርኢት፣ የሰርከስ እና የጋራ አካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ከልዩ ልዩ የመድረክ ፕሮግራሞች ጋር እንደሚቀርቡም ነዉ የተገለፀዉ።
በመድረኩ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ባለሀብቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ተማሪዎች እና አጋር ድርጅቶች የሚገኙ ሲሆን፣ ድርጅቱ ለዝግጅቱ ያዘጋጃቸውን ልዩ ቲሸርቶች በመግዛት መላው ህብረተሰብ የህፃናቱ ድምፅ እንዲሆን ጥሪ ቀርቧል።
ለዝግጅቱ የተዘጋጁ ቲሸርቶች የሚገኙበት ቦታ በቅርቡ በድርጅቱ ሚዲያዎቹ ማለትም በፈስቡክ፣ በቲክቶክ፣ ቴለግራም፣ ኢንስተግራም እንዲሁም በወብሳይቱ እንደሚያሳውቅ የተገለፀ ሲሆን፣ ፍላጎት ያላቸው ወገኖች በ 0907404111 ወይም 0906200020 በመደወል ተጨማሪ መረጃ ማግኘት እንደሚችሉ ተገልጿል።
ድርጅቱ ከተመሰረተበት ከየካቲት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት አምስት ዓመታት በቤት ለቤት ድጋፍ እና በማዕከል ደረጃ የትራንስፖርት፣ የምግብ፣ የመኝታ፣ የንፅህና እና የፊዚዮቴራፒ አገልግሎቶችን ሲሰጥ የቆየ ቢሆንም፣ በዘርፉ ያለው ግንዛቤና ተደራሽነት አሁንም አነስተኛ በመሆኑ ይህንን ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ማዘጋጀት ማስፈልጉ ተጠቅሷል።



Source: FastMereja









No comments yet.