እውቀትን ከግብረ-ገብነት ጋር ያስተሳሰረው የዙይ ሐሙሲት ከተማ ፕሮጀክት

- Advertisement -
Sidebar AD


‎📌 በዘጠኝ ወር ብቻ ግንባታው 85 በመቶ ተጠናቋል

‎ክፍል ፭

‎​#Ethiopia| በማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት በምስራቅ በለሳ ወረዳ የሚገኘው የሙት አንሳ ማር ቅዱስ ሚካኤል አንድነት ገዳም፣ መንፈሳዊ አገልግሎቱን ከማስፋፋት ባሻገር የአካባቢውን ህብረተሰብ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወት የሚቀይሩ ዘመናዊ እና ደረጃቸውን የጠበቁ የልማት ስራዎችን በስፋት በማከናወን ላይ ይገኛል።

‎የዚህ ታላቅ የልማት እንቅስቃሴ አካል የሆነውና ከገዳሙ 15 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ በሚገኘው የዙይ ሐሙሲት ከተማ የሚከናወነው ፕሮጀክት በጥቅሉ 30 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ባለው መሬት ላይ ያረፈው ሲሆን አጠቃላይ የማስተር ፕላን እቅዱን መሰረት በማድረግ ወደፊት ለሚከናወኑ ተጨማሪ የልማት ስራዎች የሚሆን ሌላ 30 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ተጠይቆለት በስፋት እየተገነባ ይገኛል።

‎​ይህ ስትራቴጂካዊ ቦታ ወደ ጎንደርም ሆነ ወደ ሰቆጣ ከተማ ለመጓዝ እጅግ አመች በመሆኑ፣ ለወደፊቱ የቀጣናው ዋና የትራንስፖርትና የእድገት መስመር እንደሚሆን ይታመናል።

‎በዚህ ቦታ ላይ የሚገነባው ዘመናዊ ትምህርት ቤት ከአንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚያስተናግድ ሲሆን፣ ዋና አላማውም የላቀ የትምህርት ጥራትን ከግብረ ገብነትና ከመንፈሳዊ ስነ-ምግባር ጋር አጣጥሞ የያዘ ትውልድ ማፍራት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው።

‎በተለይም በትምህርት ክፍሎች ውስጥ የሚኖረውን የተማሪዎች ቁጥር በመወሰን አስተማሪዎች ከእያንዳንዱ ተማሪ ጋር በቅርበት እንዲሰሩና የጥራት ክፍተቶችን እንዲቀርፉ ታስቦ የተደራጀ ሲሆን ትምህርት ቤቱ ደረጃቸውን የጠበቁ የኮምፒውተርና የሳይንስ ላቦራቶሪዎችን፣ ዘመናዊ ቤተ-መጻሕፍትን እንዲሁም የልጆችን የተፈጥሮ ተስጥኦና ስፖርታዊ ክህሎት የሚያጎለብቱ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎችን ያካተተ ነው።

‎​ከዚህ በተጨማሪም በዓለማዊውም ሆነ በመንፈሳዊው እውቀት የተካነ ትውልድን ለማፍራት ታስቦ የተደራጀው የአብነት ትምህርት ቤት ግንባታም ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል።

‎በዘመናዊ መልኩ ባለ ሶስት ፎቅ (G+3) ሆኖ የሚገነባው ይህ የአብነት ትምህርት ቤት፣ ተማሪዎቹ የመንፈሳዊውን ትምህርት እየቀሰሙ ጎን ለጎንም የዓለማዊውን ትምህርት እንዲከታተሉ የሚያደርግ ልዩ አሰራር ይከተላል።

‎ተማሪዎቹ ነፃ የመኖሪያ፣ የምግብ፣ የልብስና የመጻሕፍት አገልግሎት የሚያገኙ ሲሆን፣ የፋይናንስ እጥረት ሳይፈታተናቸው በትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ይደረጋል።

‎ከዚህም ባሻገር ከመሰረታዊ ፍላጎቶቻቸው ውጭ ያሉ ወጪዎቻቸውን የሚሸፍኑበትን ገቢ እንዲያገኙና የሙያ ክህሎት እንዲያዳብሩ፣ በገዳሙ ስር በሚገኙ የምግብ ማቀነባበሪያ፣ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ማምረቻ እና የእህል መጋዘኖች ውስጥ በትርፍ ጊዜያቸው ተቀጥረው የሚሰሩበት ምቹ ሁኔታ ተመቻችቷል።

‎​የማህበረሰቡን ጤና በመጠበቅ ረገድም ገዳሙ ትልቅ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል። በማዕከሉ ውስጥ የሚገነባው መካከለኛ ደረጃ ክሊኒክ፣ የኤክስሬይ፣ የልብ ምት መከታተሪያ ፣ የእንቅስቃሴ መከታተያ እና አልትራሳውንድ አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ የሚያሟላ በመሆኑ፣ የማህበረሰቡ አባላት ወደ ሩቅ ከተሞች በመሄድ የሚንገላቱበትን እንግልት ያስቀራል፤ እንዲሁም ለገዳሙ ተጨማሪ ገቢ ያስገኛል።

‎​የዚህ ግዙፍ ፕሮጀክት ግንባታ በታህሳስ 1 ቀን 2018 ዓ.ም. የተጀመረ ሲሆን፣ የቁሳቁስና የነዳጅ እጥረት እንዲሁም የውሃ እጥረት ቢኖርም፣ ገዳሙ የራሱን የዕንጨትና የብረት ማሽን ውጤቶች በመጠቀም ግንባታውን በጥራትና በፍጥነት በማፋጠን ላይ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት የዓለማዊ ትምህርት ቤቱ ግንባታ 85 በመቶ ያህል ተጠናቆ የመጨረሻ የማጠናቀቂያ ስራዎች እየተከናወኑለት ሲሆን፣ የአብነት ትምህርት ቤቱ የመጨረሻው ፎቅ የአርማታ ሞላ ስራ ተጠናቆ የብሎኬት ድርደራ ላይ ይገኛል።

‎ይኸው ታላቅ የልማት ፕሮጀክት የተያዘለት የጊዜ ገደብ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አቅርቦቶች ሙሉ በሙሉ ከተሟሉ በግንቦት 2019 ዓ.ም. ወይም በተጠበቀው የመጨረሻ ጊዜ እስከ ጥር 2020 ዓ.ም. ድረስ ተጠናቆ ለምዕመናንና ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች ገልጸዋል።

‎​ቀደምት ክፍሎችን ለማንበብ ከስር ያለውን ሊንክ ይጫኑ

‎​ክፍል ፩
‎https://www.facebook.com/share/p/1BaRxiEh2N/

‎​ክፍል ፪
‎https://www.facebook.com/share/p/1MXrcbSRwK/

‎​ክፍል ፫
‎https://www.facebook.com/share/p/1FymfmFJiY/

‎​ክፍል ፬
‎https://www.facebook.com/share/p/1EvDC8Yxie/

‎​አልተጠናቀቀም …..ይቀጥላል……

‎​ጌትነት ተመስገን
‎📷 ከበደ መክብብ

‎​Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

‎​#የሙትአንሳማርቅዱስሚካኤልገዳም
‎#ማዕከላዊጎንደር #ምስራቅበለሳ #getu
‎#getutemesgen #ጌጡ #EastBelesa
‎#MuteAnsaMarStMichaelMonastery
‎#CentralGondar #EthiopianOrthodoxChurch






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: