#Ethiopia | ኦክላንድ፣ ካሊፎርኒያ — ሜታ ፕላትፎርምስ (Meta Platforms) ፌስቡክንና ኢንስታግራምን ወጣቶች ሱስ እንዲይዙ አድርጎ ነድፈዋል በሚል ከቀረቡበት ክሶች ጋር በተያያዘ ከሞላ ጎደል ከሁሉም የአሜሪካ ግዛቶች ጋር ስምምነት ላይ ደርሷል።
በስምምነቱ መሠረት ሜታ ታዳጊዎች ፌስቡክን እና ኢንስታግራምን የሚጠቀሙበትን ጊዜ እና መንገድ ይገድባል።
ስምምነቱ ኩባንያው የልጆችን ደህንነት አስመልክቶ ህዝብን አሳስቷል እና ምርቶቹም በህጻናት ላይ ጉዳት አድርሰዋል በሚል የቀጠለውን የፌዴራል ፍርድ ሂደት ያቋርጠዋል ተብሏል።
ካሊፎርኒያ፣ ኮሎራዶ፣ ኬንታኪ እና ኒው ጀርሲ የተባሉት አራት ግዛቶች በክሱ ሂደት ወደ 200 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የሲቪል ቅጣት ለመጠየቅ አቅደው ነበር።
የታዳጊዎች የሶሻል ሚዲያ አጠቃቀም ይገደባል
ሜታ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ታዳጊዎች ፌስቡክን እና ኢንስታግራምን በቀን ከሁለት ሰዓት በላይ እንዳይጠቀሙ የሚያደርግ ገደብ ይጥላል። የወላጅ ፈቃድ ከሌለ ደግሞ ከእኩለ ሌሊት 6፡00 ሰዓት ድረስ አጠቃቀም ይታገዳል።
በተጨማሪም ከጠዋቱ 2፡00 እስከ 9፡00 ሰዓት ባለው የትምህርት ጊዜ አብዛኛዎቹ የገፊ የሆኑ መልዕክቶች ለታዳጊዎች እንዳይላኩ ይደረጋል። ህጻናት የእድሜ ገደብ ያላቸው ይዘቶችን እንዳያገኙም ተጨማሪ የደህንነት ርምጃዎች ይጠናከራሉ።
እነዚህ ገደቦች ስናፕቻት፣ ቲክቶክ እና ዩቲዩብ ተመሳሳይ የህጻናት ጥበቃ ርምጃዎችን ከወሰዱ የበለጠ ሊጠናከሩ ይችላሉ።
እስከ 18 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ክፍያ ሜታ ለ47 የአሜሪካ ግዛቶች፣ ለዋሺንግተን ዲሲ፣ ለፖርቶ ሪኮ፣ ለአሜሪካን ሳሞአ እና ለኖርዘርን ማሪያና ደሴቶች በአጠቃላይ እስከ 16.7 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ክፍያ ለመፈጸም ተስማምቷል።
ከዚህ ውስጥ 12.7 ቢሊዮን ዶላር የተረጋገጠ ክፍያ ሲሆን፣ ተጨማሪ 5 ቢሊዮን ዶላር ደግሞ ስናፕ፣ ቲክቶክ እና ዩቲዩብ ተመሳሳይ የህጻናት ጥበቃ ርምጃዎችን የሚወስዱበት ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ነው።
ካሊፎርኒያ ወደ 2.2 ቢሊዮን ዶላር የሚያገኝ ሲሆን፣ ኒው ዮርክ ደግሞ 1.1 ቢሊዮን ዶላር ያህል ሊያገኝ ይችላል። ቴክሳስ በበኩሉ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ የተለየ ስምምነት አድርጓል።
ከግዛቶቹ መካከል አንዳንዶቹ የሚቀበሉትን ገንዘብ በአጠቃላይ የመንግሥት ሂሳብ ላይ ለማስገባት ሲያቅዱ፣ ሌሎች ደግሞ የተወሰነውን ገንዘብ የህጻናት የአእምሮ ጤናን ለመደገፍ ለመጠቀም አቅደዋል።
የሜታ አሠራር ላይ የሚኖረው ለውጥ
የሰሜን ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፕሮፌሰር ጄምስ ስፔታ ስምምነቱ “ትልቅ ጉዳይ” መሆኑን ገልጸዋል።
እሳቸው እንደገለጹት፣ ሜታ እና ሌሎች ኩባንያዎች ክሱን ቢያሸንፉም ቢሸነፉም የንግድ አሠራራቸውን እንዲቀይሩ ከሕዝብ፣ ከኮንግረስ እና ከግዛት ሕግ አውጪዎች ጫና እየደረሰባቸው ነበር።
ሆኖም ስምምነቱ ሜታ የግል ምርጫዎችን የሚከተሉ የይዘት ምክረ ሃሳቦችን (personalized recommendations) ወይም የታለመ ማስታወቂያን (targeted advertising) እንዲያቆም አያስገድደውም።
በተጨማሪም ተመራማሪዎቹ በተለይ አሳሳቢ ናቸው ብለው የጠቀሷቸውን እንደ የሰውነት ቅርጽ ላይ አሉታዊ ስሜት የሚፈጥሩ የኢንስታግራም ጽሑፎች ያሉ አንዳንድ ይዘቶችን አይመለከትም።
ሜታ በክሱ ላይ ከስምምነትላይ ቢደርስም ጥፋት መፈጸሙን ግን አልተቀበለም። ኩባንያው የሚከፍለው ጠቅላላ ገንዘብ ከሜታ የሶስት እስከ አራት ወራት ትርፍ እና ወደ አንድ ወር ገቢ ያህል እንደሚሆን ገልጿል።
የካምብሪጅ አናሊቲካ የዳታ ጥሰት
በተለየ ጉዳይ ሜታ ከካምብሪጅ አናሊቲካ ቅሌት ጋር በተያያዙ የግላዊነት ክሶች ለመፍታት 459 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈልም ተስማምቷል። ጉዳዩ የብዙ ሚሊዮን የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የግል መረጃ ያለፈቃዳቸው መሰብሰቡን ይመለከታል።
የአሜሪካ የወረዳ ዳኛ ዮቮን ጎንዛሌዝ ሮጀርስ ዋናውን የስምምነት ሰነድ ረቡዕ ምሽት አጽድቀዋል። ዳኛዋ ከኦገስት 18 ጀምሮ የቀጠለውን የፍርድ ሂደት መርተው ነበር።
ተመሳሳይ ክሶች በመላው አሜሪካ ቀጥለዋል
ሜታ ላይ ከተመሰረቱት ክሶች በተጨማሪ በፌዴራል እና በግዛት ፍርድ ቤቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ክሶች በሶሻል ሚዲያ ኩባንያዎች ላይ ቀጥለዋል።
እነዚህ ክሶች ኩባንያዎቹ ልጆችን ሆን ብለው ወደ ሱሰኝነት የሚያመሩ ምርቶችን ነድፈዋል እና በዚህም ከጭንቀትና ከድብርት እስከ ራስን ማጥፋት የሚደርስ የአእምሮ ጤና ቀውስ አባብሰዋል የሚል ክስን ያካትታሉ።
በተጨማሪም 29 ግዛቶች ሜታ የልጆችን የግል መረጃ ያለወላጆች ፈቃድ በማሰባሰብ እና መረጃውን የጄኔሬቲቭ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ለማሰልጠን በመጠቀም በህጻናት የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንቶች ላይ ግላዊነት ጥበቃ ሕግን ጥሷል ብለው ከሰዋል።
ኒው ሜክሲኮ እና ፍሎሪዳ ከስምምነቱ ውጭ ናቸው
ኒው ሜክሲኮ በረቡዕ በተደረገው ስምምነት አልተካተተችም። የግዛቱ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ራውል ቶሬዝ ስምምነቱ አዋቂዎች ህጻናትን ላይ እንዳያነጣጥሩ የሚደረጉ ጥበቃዎችን እና ከልጆች ጋር የጾታዊ ይዘት ያለው የAI ቻትቦት ግንኙነትን ለመከልከል የሚደረጉ ርምጃዎችን አልያዘም ብለዋል።
ፍሎሪዳም ስምምነቱን አልተቀበለችም እና ክሱን በፍርድ ቤት ለመቀጠል ወስናለች። የፍሎሪዳ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጄምስ ኡዝሜየር፣ ለግዛቶች የሚከፈለው ገንዘብ ሜታ በልጆች ላይ ካደረሰው ከባድ ጉዳት ጋር ሲነጻጸር “በጣም ትንሽ” ነው በማለት ክሱን በፍርድ ቤት እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ስምምነቱ በዓለም ዙሪያ ካሉ ሌሎች ሺዎች የሚቆጠሩ በማህበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች ላይ ለቀረቡ ክሶች እንደ አብነት ሊያገለግል ይችላል ተብሏል፤ መንግስታት ደግሞ ህጻናት ጎጂ የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንቶች ላይ ይዘቶችን እንዳያገኙ ለመግታት እየሰሩ ነው፤ ከእነዚህም መካከል አውስትራሊያ ከ16 ዓመት በታች ላሉ ህጻናት ማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን ማገዷ ይታወሳል።
https://www.reuters.com/business/meta-reaches-18-billion-settlements-over-childrens-social-media-addiction-2026-08-26/
Source: GetuTemesgen









No comments yet.