የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “የኢኮኖሚ ሽብር” ሲል የገለፀውን የአሜሪካን ማዕቀብ በማውገዝ፣ ሁሉም አገራት እና መንግሥታት ማዕቀቡን ተግባራዊ ከማድረግ እንዲቆጠቡ አሳሰበ።
ሚኒስቴሩ በመግለጫው፣ አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለችውን የአንድ ወገን ማዕቀብ በመተግበር መሳተፍ የአንድን አገር “ሕገ ወጥ ፈቃድ” በሉዓላዊ አገር ላይ በመጣል ሕጋዊ የሆነውን “የኢኮኖሚ እና የንግድ ግንኙነትን ለማወክ ከመተባበር” ጋር ተመሳሳይ ነው ብሏል።
ይህም የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር የሚያረጋግጠው ‘የሉዓላዊ አገራት እኩልነት’ መርኅ ጥሰት ላይ መሳተፍ እንደሆነ መግለጫው አስረድቷል።
የአሜሪካ ማዕቀቦች “ሙሉ በሙሉ ሕገ ወጥ እና ኢ- ፍትሃዊ እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታትን ቻርተር፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግን እና የሰብዓዊ መብቶችን” የሚጥስ እንደሆነም መግለጫው ጠቅሷል።
በመሆኑም ሁሉም አገራት እና መንግሥታት ለእንደዚህ ዓይነት ማዕቀቦች ዕውቅና ከመስጠት እና ከማጽደቅ እንዲሁም ሕገ ወጥ እርምጃን ከመተግበር መቆጠብ እንዳለባቸው አሳስቧል።
ሚኒስቴሩ ጨምሮም አሜሪካ ኢራንን በኢኮኖሚ ለማግለል የወጠነችው ዕቅድ “በውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ መግባትን እና በአገራት መካከል የሚደረገውን ትብብር ማወክን” የሚከለክለውን የተባበሩት መንግሥታትን መርኅ የሚጥስ ነው ብሏል።
ሚኒስቴሩ ይህን ያለው አሜሪካ ከኢራን ጋር የንግድ ግንኙነት ባላቸው ተቋማት፣ ባንኮች እና አገራት ላይ ጭምር ማዕቀቦችን በመጣል እንደምትቀጣ ካስታወቀች በኋላ ነው።









No comments yet.