#Ethiopia | በዶክተር መዝገብ ገደፌ የተዘጋጀው በልጆች አስተዳደግ ዙሪያ የተዘጋጀው “ልጆቻችን አይሰሙንም፤ ያዩናል እንጂ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው መጽሐፍ ባሳለፍነው ሐሙስ እጅግ በርካታ እንግዶች በተገኙበት የራስ አምባ ሆቴል አዳራሽ በይፋ ተመረቀ፡፡ መጽሐፉ የወላጆች አርአያነት የልጆችን አሁናዊ እና መጪ ማንነት እንደሚቀርጽ ባማረ ቋንቋ እና ምሳሌያዊ ታሪኮች የቀረበ ሲሆን በ312 ገጾች ተቀንብቧል፡፡
የምርቃቱ መሪ ቃል “የልጆች አስተዳደግ ጉዳይን የማሕበረሰባችን መነጋገሪያ ጉዳይ እናድርገው” በሚል ሲሆን መድረኩ በታዋቂዋ ገጣሚ ረድኤት ተረፈ የተመራ ሲሆን በዝግጅቱ ላይ የጸሐፊው አብሮ አደጎች፣ የቀድሞ አስተማሪዎች.፣ የስራ ባለደረቦች ስለጸሐፊው አጠቃላይ ማንነት ንግግር ያደረጉ ሲሆን ስለመጽሐፉ አጠቃላይ ይዘት እና ስለልጆች አስተዳደግ ያላቸውን ምልከታ ደራሲ እና የሕግ አማካሪ አቶ ዳግማዊ አሰፋ፣ በመሰል ፕሮግራሞች ላይ ሐሳቦቻቸውን እና የማይጠገቡ ጨዋታዎቻቸውን በማቅረብ የሚታወቁት አቶ በኃይሉ ገብረመድኅን፣ ደራሲ ኃይለመለኮት መዋእል እና በቤተሰብ ዙሪያ በርካታ ጠቃሚ አስተዋጽኦ እያበረከቱ የሚገኙት ፓስተር ቸሬ እና የፋሚሊ ትምህርት ቤቶች እና የክቡር ኮሌጅ ባለቤት አቶ ደሳለኝ መኩሪያ በመድረኩ ላይ እይታቸውን አካፍለዋል፡፡
በመጨረሻም ለመጽሐፉ ሕትመት እና ላማረው የምርቃት ዝግጅት ውጤታማነት አስተዋጽኦ ላበረከቱ የደራሲው ወዳጆች ደራሲ ዶ/ር እንዳለጌታ ከበደ ስጦታዎችን አበርክተው የፕሮግራሙ ፍጻሜ ሆኗል፡፡
ወዳጆቻቸውን ውደዱላቸው – የወላጆች ጊዜ
ወላጆች ለልጆቻቸው ሊሰጧቻ ከሚችሉ ነገሮች ትልቁ ነገር እርስ በእርስ የሚኖራቸው ፍቅር ነው፡፡ ስለዚህም የትዳር አጋሮች ሁልጊዜም መተያየት ያለባቸው እንደ ባልና ሚስት ብቻ ሳይሆን እንደ ፍቅረኛም ነው፤ ልክ እንደዱሮው!1
· ‘ቀሪ ሀብቴ’ ተባባሉ፡ ዘወትር የፍቅር ቃላት መለዋወጥን፤ ባገኛችሁት አጋጣሚ ሁሉ መተቃቀፍን፣ መሳሳምን፣ መቀላለድን እና በፍቅር ዐይን መተያየትን ልማድ አድርጉ። ‘አብራ ኗሪዬ’፣ ‘አብሮ ኗሪዬ’ ተባባሉ።
· ‘ያዥልኝ/ያዝልኝ ቀጠሮ’ ተባባሉ፡ ያላችሁን ትርፍ ጊዜ አብቃቅታችሁ ከቤት ውጪ ተቀጣጥራችሁ ዘና ያለ የብቻ ጊዜ አሳልፉ። ልጆቻችሁም ሆነ ሌሎች ሰዎች ይህንን ጊዜያችሁን እንዲሻሙባችሁ አትፍቀዱ። ይህ ፍቅራችሁን ያድስላችኋል። በተጨማሪም በልጆችም ሆነ በሌላ ቤተሰባዊ ጉዳይ ላይ ትኩረት የተሞላበት ውይይት እንድታደርጉ ያስችላችኋል። ስለዚህ ‘ያዥልኝ ቀጠሮ’፣ ‘ያዝልኝ ቀጠሮ’ ተባባሉና ወጣ ብላችሁ ተጨዋወቱ። ተዝናኑ።
· ‘በስልክ አነጋግረኝ’ ይበሉ: የብቻ ጊዜ ቢጠፋ እንኳን በስልክ ረዘም ላሉ ሰዓታት ማውራትም አንዱ መፍትሔ ነው። ውድ ወላጅ የልጅዎን አባት “በስልክ አነጋግረኝ፤ በቀጭኑ ሽቦ” ይበሉት። ካልሆነ ግን “ትወደኝ አትወደኝ አላውቅም” መባባል ይመጣል።
ከመጽሐፉ የተቀነጨበ
ደራሲው ዶ/ር መዝገብ ገደፌን
Facebook- Mezgeb Gedefe Molla (https://www.facebook.com/mezgeb.molla)
Linkdin፡ Mezgeb Gedefe
ላይ ብትከታተሏቸው በርካታ ጠቃሚና ሳይንሳዊ የልጅ አስተዳደግ መርሆችን ታገኛላችሁ፡፡
ለበለጠ መረጃ፡ 0944724444 / 0911563764/ 0911149869



Source: GetuTemesgen








No comments yet.