ደባርቅ ከ450 ሚሊዮን ብር በላይ ለኮሪደር ልማት ማሰባሰቧን አስታወቀች።

- Advertisement -
Sidebar AD


‎ደባርቅ ከተማን የቱሪዝም መዳረሻነቷን ለማሳደግ የተጀመረው የኮሪደር ልማት እንቅስቃሴ ከፍተኛ ድጋፍ እያገኘ መሆኑ ተገለጸ።

‎ባሳለፍነው ሳምንት ነሐሴ 18/2018 ዓ.ም በተካሄደው ታላቅ የሃብት ማሰባሰቢያ መድረክ፣ ደባርቅን የበለጠ ዘመናዊ፣ ማራኪና ለቱሪዝም ምቹ ከተማ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ትልቅ የህዝብና የባለሃብቶች ድጋፍ አግኝቷል።

‎በመርሃ ግብሩ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀሥላሴ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ እንዳለው መኮንን፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት አረጋ ከበደ፣ የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ቻላቸው ደኘው፣ የሰሜን ጎንደር ዋና አስተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ፣ የደባርቅ ከተማ ከንቲባ አቶ ኔትነት ፀጋየ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ባለሃብቶችና እንግዶች ተገኝተዋል።

‎በመድረኩ ተሳታፊዎች ለደባርቅ ያላቸውን አጋርነት በተግባር በማሳየታቸው፣ ከ450 ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብና በአይነት ማሰባሰብ ተችሏል። የልገሳ ሂደቱ አሁንም በመቀጠሉ የተሰበሰበው ሃብት ወደፊት የበለጠ ሊጨምር እንደሚችልም ተጠቁሟል።

‎በእዚህ የገንዘብ ማሰባሰብ ላይ ወጣቱ ባለሀብት የሬማ ኮንስትራክሽን ባለቤት አቶ ፍቅሬ 20 ሚሊየን ብር፣ አቶ በላይነህ ክንዴ 10 ሚሊየን ብር ፣ ቢአይካ 15 ሚሊየን ብር እና ሌሎችም ባለሀብቶች ከፍተኛ ተሳትፎ አድርገዋል።

‎ይህ እንቅስቃሴ ደባርቅን ከከተማ ልማት ባለፈ በቱሪዝም፣ በኢንቨስትመንትና በንግድ ዘርፎች የሚኖራትን ሚና ለማጠናከር ዕድል እንደሚፈጥር ተገልጿል። ከተማዋም በክልልና በሀገር አቀፍ ደረጃ የበለጠ ትኩረት በማግኘት የመንግስትና የግል ሚዲያዎችን ቀልብ መሳቧ ታውቋል።

‎በመድረኩም ባለሃብቶች በደባርቅና በሰሜን አካባቢዎች በሚኖሩ የኢንቨስትመንት ዕድሎች በመሳተፍ የአካባቢውን ልማት እንዲያግዙ ጥሪ ቀርቧል።

‎የአሁኑ የሃብት ማሰባሰቢያ መድረክ በከፍተኛ ባለስልጣናትና በታዋቂ ባለሃብቶች ደረጃ የተካሄደ መሆኑን የገለጸው የደባርቅ ከተማ ልማት ኮሚቴ፣ ቀጣዩ የልማት ምዕራፍ ግን የከተማዋን ነዋሪዎችና ደባርቅን የሚወዱ ሁሉንም አካላት የሚያሳትፍ እንዲሆን ከወዲሁ ተነግሯል።







Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2