#Ethiopia | በአዲስ አበባ ከተማ በጥርስ ሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ የላቀ አፈፃፀምና ብቃት ላሳዩ የጥርስ ሕክምና ተቋማትና ባለሙያዎች እውቅና የሚያሸልም አዲስ መድረክ ይፋ ተደረገ።
የእውቅና መርሐግብር የተዘጋጀው በአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን እና ሮባ መልቲሚዲያና ኢቨንትስ በቅንጅት ነው።
የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ሙሉእመቤት ታደሰ እንደገለጹት፣ የመስሪያ ቤታቸው ዋነኛ ዓላማ የሕክምና፣ የምግብና ጤና ነክ ተቋማትን አገልግሎትና ምርት ጥራት ማስጠበቅ እንዲሁም የኅብረተሰቡን የመኖር እድሜ ጣሪያ ከፍ ማድረግ ነው።
ዶክተር ሙሉእመቤት አክለውም እንደተናገሩት፣ ባለሥልጣኑ ተቋማትን ከመቆጣጠር፣ ፈቃድ ከመስጠትና ሕግ ከማስከበር ባሻገር በጥርስ ሕክምና ዘርፍ የላቀ አገልግሎት የሚሰጡትን ማበረታታት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ይህ የሽልማት ፕሮግራም ተዘጋጅቷል ብለዋል።
በከተማዋ ያሉ የስፔሻሊቲ የጥርስ ሕክምና ክሊኒኮች በ2018 ዓ.ም ባሳዩት የሥራ አፈፃፀም የሚመዘኑበት ይህ መድረክ፣ ባለሙያዎች ለጥራትና ለበለጠ ብቃት እንዲተጉ ትልቅ ተነሳሽነት ይፈጥራል።
እንደ ዶክተር ሙሉእመቤት ገለፃ፣ አጠቃላይ የዳኝነት ሂደቱ በሁለት መለኪያዎች ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ 75 ፐርሰንቱን የኢትዮጵያ ስታንዳርድ ኤጀንሲን መስፈርት ተከተሎ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ በሙያዊ ምዘና የሚሰጠው ሲሆን፣ ቀሪውን 30 ፐርሰንት ደግሞ አገልግሎቱን የሚያገኙት የኅብረተሰብ ክፍሎች በድምፅ የሚሰጡት ይሆናል።
በዚህም መሠረት በ15 የተለያዩ ዘርፎች የላቀ አፈፃፀም ያሳዩ ተቋማት ተለይተው እውቅና ይሰጣቸዋል።
ዶክተር ሙሉእመቤት አብራርተው እንደተናገሩት፣ የአፍና ጥርስ ጤና አጠባበቅ አጠቃላይ የሰውነት ጤናንና ውበትን ለመጠበቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው ቢሆንም፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ ገና ሰፊ የግንዛቤ ክፍተት ይታያል።
በመሆኑም ይህ መርሃ ግብር የሕክምና ተቋማት አገልግሎታቸውንና ብቃታቸውን ለሕዝብ የሚያስተዋውቁበት ዕድል የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ፣ ሕዝቡ ስለ ጥርስ ጤና አጠባበቅና ሕክምና በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጥ ያግዛል።
በመጨረሻም ዶክተር ሙሉእመቤት እንደገለጹት፣ ይህ መድረክ የሀገር ውስጥ አገልግሎትን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግና ከአፍሪካ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ተወዳዳሪ የሆኑ የጥርስ ሕክምና ማዕከላትን ለማፍራት ትልቅ መነሻ ይሆናል።
ይህ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነው የእውቅና ፕሮግራም በየዓመቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም በመድረኩ ላይ ተገልጿል።
በጌትነት ተመስገን
#DentalCareEthiopia #DentalClinicAddis
#AAFDA #HealthAwardsEthiopia
#DentalHealth #MedicalTourismEthiopia
#AddisAbabaHealth




Source: GetuTemesgen








No comments yet.