ዓባይ ቴሌቪዥን ማስጠንቀቂያ ተሰጠው

- Advertisement -
Sidebar AD

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን በዓባይ ቴሌቪዥን ላይ ባካሄደው የሚዲያ ሞኒተሪንግ የሕግና የጋዜጠኝነት ሙያ ስነ-ምግባር ጥሰቶች መፈጸማቸውን በማረጋገጡ ለጣቢያው ጥብቅ የማስጠንቀቂያ መመሪያ አስተላለፈ።

የቴሌቪዥን ጣቢያው አመራሮች በበኩላቸው በቁጥጥር ሂደቱ የቀረቡትን ግምገማዎች ሙሉ በሙሉ አዎንታዊ በሆነ መንገድ በመቀበል ለተከሰቱት ስህተቶች ይቅርታ በመጠየቅ አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወስዱ አስታውቀዋል።

​ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባለፉት ሦስት ወራት ማለትም ከሰኔ እስከ ነሐሴ 2018 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በጣቢያው በተላለፉ ዜናዎች ፕሮግራሞችና ማስታወቂያዎች ላይ ባደረገው የይዘት ክትትል፣ ከማህበረሰቡ ባህልና እሴት ያፈነገጡ ፀያፍ ንግግሮች፣ የወጣቶችን ስነ-ምግባር የሚያበላሹና የሴቶችን ክብር የሚነኩ ይዘቶች መተላለፋቸውን አረጋግጧል።

በተጨማሪም በዜና አሰራር ላይ ያልተረጋገጡ የመረጃ ምንጮችን መጠቀም ሌላው የታየ ዋና ግድፈት መሆኑ ተጠቅሷል።

​የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኃይማኖት ዘለቀ ከጣቢያው ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ዓባይ ቴሌቪዥን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙና የሀገርን ጥቅም የሚያስቀድሙ ይዘቶችን በማቅረብ የሚታወቅ የንግድ ሚዲያ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋሉ የህግና የሙያ ስነ-ምግባር ጥሰቶች ግን በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌላቸው መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

አክለውም ጣቢያው የመገናኛ ብዙኃን አዋጁንና የጋዜጠኝነት ሙያ መርሆዎችን ከኤዲቶሪያል ፖሊሲው ጋር በማቀናጀት አፋጣኝ እርምት እንዲያደርግ አሳስበዋል።

​የዓባይ ቴሌቪዥን ኃላፊዎች በበኩላቸው በባለስልጣኑ የቀረቡትን አብዛኛዎቹን ግድፈቶች ጣቢያቸው አስቀድሞ በኤዲቶሪያል ደረጃ ገምግሟቸው የነበሩ መሆናቸውን ገልጸው፣ የተሰጣቸውን አስተያየት በፍጥነት በማረም ተግባራዊ ለማድረግ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።

አክለውም ጣቢያው አገራዊ መልካም ተሞክሮዎች የሚቀርቡበትና በስነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ የሚገነባበት ይዘት ይዞ እንዲቀጥል የተሰነቀውን ራዕይ በቁርጠኝነት እንደሚተገብሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን


Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: