#Fastmereja:-በኢትዮጵያ የሚገኙ ተማሪዎች ባሉበት ቦታ ሆነው በስልካቸው በቀላሉ ዘመናዊና አሳታፊ ትምህርት እንዲያገኙ የሚያስችል “MySeed” የተሰኘ የትምህርት ሞባይል መተግበሪያ በዛሬው ዕለት በይፋ ተመረቀ።
በማህበራዊ ሚዲያ “ቲቸር ዳኒ” በሚል ስም የሚታወቁት የመተግበሪያው መስራች ዳኛቸው ሻምበል እንደገለጹት፤ የመተግበሪያው ዋና ዓላማ በገጠርም ሆነ በከተማ የሚገኙ ተማሪዎች በየቤታቸው ሆነው በእጃቸው ባለው ስልክ በቀላሉ ተምረው ካሰቡበት የትምህርት ደረጃ እንዲደርሱ ማስቻል ነው ሲሉ ገልፀዋል።
አቶ ዳኛቸዉ አክሎም ትምህርቶቹ ከተለመደው የክፍል ውስጥ የማስተማር ዘዴ በተለየ መልኩ እንደ ፊልም በተመራ አቀራረብ (Directed) ተማሪዎች ተዝናንተው እንዲማሩ ሆነው በቪዲዮ የተቀረጹ ስለመሆናቸዉም ነዉ ያስረዱት።
አፕሊኬሽኑ ከ5ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች የተዘጋጀ ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ (11ኛ እና 12ኛ ክፍል) ለተፈጥሮ ሳይንስ እና ማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ሁሉንም የትምህርት ዓይነቶች አሟልቶ መያዙ ተገልጿል።
ይህ አፕሊኬሽን ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ የአስተሳሰብ (Mindset) ስልጠናዎችን እና ተማሪዎች ለወደፊት የሙያ ህልማቸው እንዲዘጋጁ የሚያስችሉ መሪ ትምህርቶች በአፕሊኬሽኑ መካተታቸው ተጠቅሷል።
እንዲሁም ተማሪዎች በወር 399 ብር ክፍያ በመፈጸም የቪዲዮ ትምህርቶችን፣ የፒዲኤፍ (PDF) ማስታወሻዎችን እና የልምምድ ጥያቄዎችን ማግኘት እንደሚችሉም ተገልጿል።
በተጨማሪም በወር ተማሪዎች ቪዲዮዎችን አንድ ጊዜ ዳውንሎድ ካደረጉ በኋላ ያለ ምንም ተጨማሪ የኢንተርኔት ዳታ ዓመቱን ሙሉ በኦፍላይን (Offline) መከታተል የሚያስችላቸው አሰራር የተዘረጋ ሲሆን በዓመቱ መጨረሻ በመተግበሪያው ከፍተኛ ውጤት ለሚያመጡ ተማሪዎች የሚሰጥ የመኪና ሽልማት የተዘጋጀ መሆኑም ተበስሯል።
አፕሊኬሽኑ በአሁኑ ወቅት በGoogle Play Store እና App Store ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን እንዲሁም በቀጣይም ከሶስት ወራት በኋላ ትምህርቱን በሌሎች አራት የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ተዳራሽ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገልጻል።



Source: FastMereja








No comments yet.