#FastMereja I በኡጋንዳ ካምፓላ ከነሐሴ 27 እስከ 29 ቀን 2018 ዓ.ም (እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ኦገስት 2026) በተካሄደው አህጉራዊ የወጣቶች በተግባር ላይ ስብሰባ፣ የቤተር ላይፍ ፎር ኦል መስራችና ዋና ዳይሬክተር አቶ ከተማ ባህሩ የ2026 የወጣቶች ተሳትፎ ለዘላቂ ልማት ግቦች ሽልማት ተሸላሚ ሆነዋል። አቶ ከተማ ይህንን ታላቅ አህጉራዊ እውቅና ያገኙት በወጣቶች አቅም ግንባታ፣ በማህበረሰብ አገልግሎት፣ በአጋርነት ግንባታ እና በዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት ላይ ላሳዩት የላቀ አመራርና ላበረከቱት አስተዋፅኦ ነው።
የዘመኑን አህጉራዊ የወጣቶች እንቅስቃሴና የልማት ስልቶችን መሠረት በማድረግ በተዘጋጀው በዚህ መድረክ ላይ የተሰጠው እውቅና፣ ወጣቶች በልማት አጀንዳዎች ላይ ከተራ ተሳታፊነት አልፈው ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡ መሪዎች መሆን እንደሚችሉ ማረጋገጫ ተደርጎ ተወስዷል። መድረኩ የወጣቶችን አመራር ለማጠናከር፣ ተቋማዊ አጋርነትን ለማስፋፋት እና በየደረጃው ዘላቂ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ተግባራትን ለማፋጠን ያለመ አህጉራዊ ንቅናቄ አካል ነው።
አቶ ከተማ ባህሩ ሽልማቱን ከተቀበሉ በኋላ ባስተላለፉት መልእክት፣ ይህ እውቅና የጋራ ጥረት ውጤት መሆኑን ገልጸው በቀጣይም ወጣቶችን ለማብቃት፣ ጠንካራ አጋርነቶችን ለመፍጠር እና ማህበረሰቦችን ለማገልገል ያላቸውን ቁርጠኝነት አድሰዋል። ይህ ስኬት ለኢትዮጵያውያንና ለአፍሪካውያን ወጣቶች በአህጉራዊ መድረክ የተሰጠ ትልቅ እውቅና እና ማበረታቻ እንደሆነ ተነግሯል።

Source: FastMereja









No comments yet.