የቴሌብር ደንበኞች ቁጥር ከ60 ሚሊዮን በላይ ደርሷል

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | እስከ 2020 ዓ.ም ድረስ የቴሌኮም ተጠቃሚዎችን ቁጥር 100 ሚሊዮን ማድረስ፣ የቴሌብር ተጠቃሚዎችን ቁጥር ወደ 75 ሚሊዮን ለማድረስ እየሰራን እንገኛለን ተብሏል።

ኢትዮ ቴሌኮም የቀጣዩ አድማስ ስትራቴጂ የአንድ ዓመት ጉዞ እና የሁለተኛ ዓመት ዕቅድን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፣ ስትራቴጂው ለሦስት ዓመት ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውሰዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም ከ2018 እስከ 2020 ዓ.ም ድረስ ተግባራዊ የሚደረግ የሦስት ዓመት አጠቃላይ የዲጂታል ልማት ዕቅድ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ስትራቴጂው ኢትዮጵያ በአፍሪካ የዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ የመሪነት ሚና መጫወት የሚያስችላት መሆኑን ተናግረዋል።

የዜጎችን ሁለንተናዊ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም የሚሆነው ይህ ስትራቴጂ ዘርፈ ብዙ ተደራሽነትን በማረጋገጥ የቴሌኮም እና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ማስፋፋት የሚያስችል መሆኑም ተነሥቷል።

የቀጣዩ አድማስ ስትራቴጂ ትግበራ የመጀመሪያው ዓመት 215 ቢሊዮን ብር ገቢ የተገኘበት ነው።

በስትራቴጂው ማጠናቀቂያ የደንበኞችን ቁጥር ወደ 90 ሚሊዮን የማድረስ ዕቅድ ሲኖር፣ የቴሌብር ደንበኞችንም ቁጥር ከ60 ሚሊዮን በላይ ደርሷል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገለጻ፣ የስትራቴጂው ግብ ኩባንያውን ከተለመደ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ኩባንያ መቀየር ነው።

ደንበኛ ተኮር ዲጂታል አገልግሎት የቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የተደገፈ የሥራ ቅልጥፍና፣ የንግድ ሥርዓቱን ማዘመን፣ የሰው ኃይል ማጠናከር እና ዘላቂነት እና አረንጓዴ ዕድገትን ማጠናከር የስትራቴጂው ዋና ዋና ግቦቹ ናቸው።

እስከ 2020 ዓ.ም ድረስ የቴሌኮም ተጠቃሚዎችን ቁጥር 100 ሚሊዮን ማድረስ፣ የቴሌብር ተጠቃሚዎችን ቁጥር ወደ 75 ሚሊዮን፣ የ4G ሽፋንን ወደ 85% ማሳደግ እና የ5Gን አገልግሎት ወደ ተጨማሪ ከተሞች ማስፋፋት እና የአሮጌ የኮፐር መስመሮችን በፋይበር መተካት ዋና ዋና ግቦች ናቸው።

ስትራቴጂው ከቁጥር ባሻገር ሰው ተኮር ልማት ነው ያሉት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፣ በመሆኑም ስትራቴጂው ሲጠናቀቅ ከ2.6 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ያስችላል ብለዋል።

ሔኖክ ወ/ገብርኤል

#Ethiopia #GetuTemesgen





Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2