ያሆዴ — የሀዲያ ሕዝብ የአዲስ ዘመን፣ የምስጋናና የተስፋ በዓል

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | የሀዲያ ሕዝብ በረጅም የታሪክ ጉዞው ያዳበረው ጽኑ ማንነት፣ ቋንቋ፣ እምነትና ባህላዊ አኗኗር መገለጫ ከሆኑት ድንቅ ቅርሶች መካከል የያሆዴ በዓል አንዱና ዋነኛው ነው።

የስያሜው ምስጢርና ትርጉም

“ያሆዴ” የሚለው ስያሜ በበዓሉ ወቅት ከሚሰማው “ያሆሆሆ” የሚለው የዜማ ቅላጼ እና “ኤዴ” ከሚለው ጥምር ቃል የተገኘ መሆኑ ይነገራል።

“ኤዴ” ማገናኘት፣ ማጣመርና ማያያዝ የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን፣ ይህም በዓሉ ማህበረሰቡን ከአዲስ ልምላሜ፣ ከተስፋ፣ ከሰላምና ከብርሃን ጋር የሚያስተሳስር ድልድይ መሆኑን ያመለክታል።

የዘመን ስሌትና የተፈጥሮ ምልክቶች

የሀዲያ አባቶች ያለ ዘመናዊ የሳይንስ መሳሪያ የተፈጥሮን ምልክቶች በመመልከት የዘመን መለወጫን ያሰሉ ነበር። የከዋክብትን ጉዞ፣ የጨረቃን ዑደት፣ የንፋስን አቅጣጫ፣ የወፎችን ዝማሬና የወንዞችን ሙላት በመመርመር የአዲሱን ዘመን መምጣት ያረጋግጡ ነበር።

በተጨማሪም ወደ ጥበብ አዋቂዎቹ Hiraagaano / ህራጋኖ በመሄድ የአዲሱን ዓመት ብስራት ያረጋግጣሉ።

Aganchi Yabaraakko — የጨረቃዋ መፈንጠቅ

የክረምቱን ድቅድቅ ጨለማ ገፋ በወርቃማ ድምቀት ብቅ ስትል፣ ሕዝቡ በአንድ ድምፅ፦

“ጨረቃዋ ፈነጠቀች!”

በማለት በደስታ ይቀበላታል።

ዘራሮዕ-ፊታ

ማንም ሳይዘራው፣ በሰው ሰራሽ መስኖም ሆነ በበጋ ዝናብ ሳይበቅል፣ ያሆዴ ሲደርስ ወቅቱን ጠብቆ የሚፈነዳው ይህ ብርቅዬ አበባ የአዲስ ዘመን መባቻ ዋነኛ ማብሰሪያ ነው። አባቶችም ለተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች ይጠቀሙበታል።

የበዓሉ ድምቀትና ማህበራዊ እሴት

ያሆዴ የሰው ልጆች ብቻ ሳይሆኑ የተፈጥሮ ፍጥረታትም የሚታደሱበት የደስታና የተስፋ ወቅት ነው።

የእንስሳት ደስታ፦
ለወራት በጥበቃ ታሽጎ የቆየው ኩቱራ (Kutura) ለምለም የግጦሽ መሬት ሲከፈት፣ ከብቶች በነፃነት ይቦርቁበታል።

የማዕድና የህብረት ፌሽታ፦
ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች ተዘጋጅተው፣ ዘመድ አዝማድና ጎረቤት በአንድነት ይቋደሳሉ።

ዕርቅና ጋብቻ፦
ያሆዴ ከጨለማ ወደ ብርሃን የመሸጋገሪያ ወቅት ብቻ ሳይሆን፣ የተጣላ የሚታረቅበት፣ የተራራቀ የሚገናኝበት እና ለትዳር የበቁ ወጣቶች የሚተጫጩበት ማህበራዊ መድረክ ነው።

ያሆዴ የአዲስ መጀመሪያ ምልክት ነው።
ያለፈውን በምስጋና ተቀብሎ፣ የወደፊቱን በተስፋ የሚመለከትበት፤ ቤተሰብ የሚቀራረብበት፣ ሰላም የሚሰፍንበትና ማንነት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍበት ታላቅ ባህላዊ ቅርስ ነው።

የቀደምት አባቶች በጥልቅ ጥበብና ማስተዋል የቀመሩትን ይህን የአዲስ ዘመን፣ የምስጋናና የተስፋ በዓል ማንነቱን ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ የሁላችንም የጋራ ኃላፊነት ነው።

✍️ ናኒ ከሆሳዕና

#ያሆዴ #ሀዲያ #Hadiya #Yahode #Hossana #የኢትዮጵያባህል #የባህልቅርስ #የአዲስዘመን #EthiopianCulture​#heritage #yahodefestival #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2