የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣንና መልቲቾይስ አፍሪካ በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ቅጅና ተ

- Advertisement -
Sidebar AD

የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣንና መልቲቾይስ አፍሪካ በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃና ግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሶስትዮሽ የትብብር መግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

በኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ፈጠራዎች ቅጅና ተዛማጅ መብቶች እንዲጠበቁ፣ ግንዛቤ ለማስጨበጥና የፊልምና ተያያዥ ጥበባት ባለሙያዎች፣ ተቋማትና ሀገር ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ዓላማ በማድረግ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣንና መልቲቾይስ አፍሪካ በጋራ ለመስራት የሶስትዮሽ የትብብር መግባቢያ ስምምነት ፊርማ ተፈራርመዋል።

ይህ የሶስትዮሽ ስምምነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥሰት በጋራ ለመከላከል፣ የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ኪነ ጥበባዊ ፈጠራዎች የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ እንዲያገኙ ለማስቻል ጉልህ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ታምኖበታል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እምቅ የሆነውን የኢትዮጵያን የባህል፣ የታሪክ፣ የኪነ ጥበብ ፣ የስነ ጥበብ ፈጠራዎች ሁለንተናዊ እድገት እንዲኖራቸውና እንዲተዋወቁ ትኩረት ተሰጥቶ እየሰራ ይገኛል። የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን በበኩሉ የአዕምሯዊ ንብረት ህጎች ፣ የቅጅ መብቶች፣ የንግድ ምልክቶችና ፓተንቶች ተገቢውን ጥበቃ እንዲያገኙና ግንዛቤ እንዲጎለብት እየሰራ የሚገኝ መንግስታዊ ተቋም ነው። መልቲቾይስ አፍሪካ ሆልንዲንግ ደግሞ በአፍሪካ ግዙፍና የላቀ ጥራት ያላቸውን የመዝናኛና ስፖርት ይዘቶች ለደንበኞች የሚያቀርብ አህጉራዊ ተቋም ሲሆን ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ለሚጠጉ ጊዜያትም ለኢትዮጵያውያን የመዝናኛና ስፖርት ይዘቶች አፍቃሪያን እያቀረበ ይገኛል።

ባለፉት ጊዜያት እነዚህ ሶስቱ ተቋማት በመልቲቾይስ አፍሪካ አህጉር ተኮር ፕሮጀክት በሆነው Partners Against Piracy (PAP) አማካኝነት ከባለድርሻዎች ጋር የይዘቶች ቅጅና ተዛማጅ መብቶች ዙሪያ ያተኮሩ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እየሰሩ የነበረ ሲሆን ያ ትብብር አድጎና ጎልብቶ ወደ ሶስትዮሽ የትብብር መግባቢያ ስምምነት ፊርማ ደርሷል። ይህም ተቋማቱ የቅጅና ተዛማጅ መብት ጥሰትን ለመከላከልና የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያላቸውን ቁርጠኝነት ከማሳየቱም በላይ የቅጅና ተዛማጅ መብት ጥሰት በሀገር ኢኮኖሚ ፣ በባለሙያውና በዘርፉ ኢንቨስት እያደረጉ ባሉ ተቋማት ላይ እያደረሰ ያለው ተፅዕኖ በትብብር ለመከላከልና ባለድርሻዎችን ለማስተባበር ያላቸውን ተነሳሽነትም የሚያረጋግጥ ነው።

ዛሬ የተፈረመው የሶስትዮሽ የትብብር መግባቢያ ሰነዱም በ ዋናነት ያተኮረባቸው፦

የተለያዩ የብዙኃን መገናኛ ዘዴዎችንና ሌሎች መንገዶችን በመጠቀም የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎችን በጋራ ለመስራት፣
በቅጅና ተዛማጅ መብት ጥሰት የተሰማሩ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን በጋራ ለህግ ተጠያቂነት ለማቅረብ፣

በቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት የተለያዩ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎችን ለማዘጋጀትና የልምድ ልውውጦችን ለማመቻቸት፣ እንዲሁም

የቅጅና ተዛማጅ መብቶችን ጥበቃ የሚያስከብሩት የህግ ማዕቀፎች እንዲከበሩ ለማድረግና ከሚመለከታቸው የፍትህ አካላት ጋር በትብብር ለመስራት ናቸው።

ይህንን አስመልክቶ ክብርት ነፊሳ አልመህዲ ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ የባህልና ኪነ ጥበባዊ ፈጠራዎችን መጠበቅ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው። ይህ ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣንና ከመልቲቾይስ አፍሪካ ጋር የተፈራረምነው የሶስትዮሽ የትብብር መግባቢያ ሰነድም ለዘርፉ ባለሙያዎች የፈጠራ ይዘቶቻቸው ተጠቃሚነትና የኢትዮጵያን የባህልና ኪነ ጥበብ ፈጠራዎችን ለመጠበቅም ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው እምነት አለኝ” ብለዋል።

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ እንዳሉ ሞሲሳ በበኩላቸው ” መስሪያ ቤታችን የቅጅና ተዛማጅ መብቶች እንዲከበሩና የፈጠራ ባለሙያዎች ከመብት ጥሰት ስጋት ነፃ እንዲሆኑ ምቹ ከባቢን ለመፍጠር ራዕይ ሰንቆ እየሰራ ነው። ይህንን የሶስትዮሽ የጋራ ትብብር መግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም ስንነሳም ባለስልጣን መስሪያ ቤታችን ከተቋቋመለት ዓላማ ጋር የሚሰናሰል በመሆኑና ግንዛቤ በማስጨበጥም ሆነ የቅጅና ተዛማጅ መብት ጉዳይ የህግ ማዕቀፎች እንዲከበሩ የማስቻል ኃላፊነት ስላለብን ነው” ብለዋል።

የመልቲቾይስ አፍሪካ ሆልዲንግ የሬጉላቶሪና ኮርፖሬት ጉዳዮች ግሩፕ ኤክስኪዩቲቭ ዶ/ር ኪያቤትስዌ ሞዲሞንግ ” ሶስቱ ተቋማት ከዚህ በፊትካደረጓቸው የጋራ ትብብር ስራዎች በዘለለ ትብብራቸውን ወደ ሌላ ምዕራፍ ያሸጋገረ ነው። እኛ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ላለን ሁለንተና የማህበራዊና ቢዝነስ ዕድገት ቁልፍ መዳረሻ አድርገን ነው የምናያት። ለሰላሳ ዓመታት ለሚጠጉ ጊዜያትም ከኢትዮጵያውያን የስፖርትና መዝናኛ አፍቃሪያን ጋር ቁርኝት በመፍጠራችን ክብር ይሰማናል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህም ሀገራዊ ይዘቶችን እያቀረብን ሲሆን ከ200 በላይ ከሚሆኑ የኢትዮጵያ ፕሮዳክሽን ድርጅቶች ጋር ሰርተናል ፣ እየሰራንም ነው። በመልቲቾይስ ታለንት ፋክተሪ ስኮላርሺፕ አማካይነትም ኢትዮጵያውያን ወጣት የፊልም ጥበብ ባለሙያዎች ተጠቃሚ እያደረግን ነው። የቅጅና ተዛማጅ መብትን በተመለከተ ከኢትዮጵያ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ጋር በትብብር ለመስራት ይህንን መግባቢያ ስምምነት ስንፈርም በይዘት መብቶች ጥበቃ ዙሪያ ያለንን ቁርጠኝነት ለማረጋገጥ ነው” ብለዋል።

ዛሬ በሶስቱ ተቋማት የተፈረመው የኪነ ጥበብ ቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥሰትን የመከላከልና በጉዳዩ ዙሪያ የተለያዩ ትብብሮችን በጋራ መስራት በየቅጅ መብትን በተሻለ መልኩ እንዲጠበቅ በማድረግና ሌሎች ባለድርሻዎችንም ለማስተባበር ብሎም ለባለሙያው ተጠቃሚነት እንዲሁም ለሀገር ኢኮኖሚና ገፅታ ግንባታ የጎላ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።





Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2