የኢትዮጵያ አባቶች ቀን “ክብር ለአባትነት” በሚል በወጣቱ የጥበብ ባለሙያ እና በጎ አድራጊ እዮብ አርጋው ሃሳብ አመንጪነት የኢትዮጵያ አባቶች ቀን የበጎ አድራጎት ማህበር ያስጀመረው በሃገሪቱ ቀዳሚና ብቸኛ በሆነ መልኩ ልክ እንደ “የእናቶች ቀን” ሁሉ የአባቶች ቀንም በየአመቱ ግንቦት 15 ኢትዮጵያዊ አባትነትን የሚመጥን መልክ ሰጥቶ ማክበርን የጀመረ ነው።
ይህ የኢትዮጵያ አባቶች ቀን ኢትዮጵያውያን በራሳችን ወግና እሴት ብሎም የመከባበር ባህል መሰረት ኢትዮጵያዊ ቀለም ባለው መልኩ “ክብር ለአባትነት” በሚል ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በየአመቱ ግንቦት 15 በሃገር አቀፍ ደረጃ መከበር የጀመረ ነው።
ይህ ግንቦት 15 የተመረጠበት ምክንያት የጣልያን ወራሪ ኃይልን አድዋ ላይ መክተው ያሸነፉት ጀግኖች አባቶቻችን በድል አድራጊነት ወደመናገሻ ከተማቸው የተመለሱበት በመሆኑ ብዙሃኑ አባቶች ከቤተሰብ ባሻገር ለሃገር መፅናት ላደረጉት ተግባር የሚታወሱበትና ምስጋና የሚቀርብበት ዕለት እንዲሆንም በማሰብ ነው፡፡
ላለፉት 17 አመታት በኢትዮጵያ የአባቶች ቀንን ግንቦት 15 ላይ ሲያከብር በቤተሰባቸው፣ በአካባቢያቸው፣ በወዳጆቻቸው እና በዙሪያቸው ባሉ ሁሉ ስማቸው በመልካም የሚነሳ፣ አርአያ መሆን የቻሉ፣ ከቤተሰብ እስከ ሃገር በመልካም አባትነትና አበርክቶ የሚነሱ አባቶችን፤ የኢትዮጵያ አባቶች የክብር መገለጫ የሆነውን ጋቢ በመደረብ፣ ዝቅ ብሎ እግር በማጠብ፣ የዕውቅና ምስክር ወረቀት በመስጠትና ታሪካቸውን በመሰነድ ሲያመሰግን እና ሲያከብር ቆይቷል።
እስካሁን እነማን ተመሰገኑ?
የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዝደንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ጄኔራል ጃገማ ኬሎ፣ ሰዓሊ አለ ፈለገ ሰላም፣ ሰዓሊ ለማ ጉያ፣ ጋሽ አለማየሁ ፈንታ፣ ዶ/ር ተወልደ ገብረእግዚአብሔር፣ ዶ/ር ሽመልስ አዱኛ፣ ደራሲ ማሞ ውድነህ፣ ፕሮፌሰር አብይ ፎርድ፣ የባህል ህክምና ባለሙያው ሀኪም ማሞ እንዲሁም የጋሞ የሃገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የመኖሪያ ቤትና የድርጅት የጥበቃ ሰራተኛ ሆነው እያገለገሉ ከሚገኙ በአነስተኛ ገቢ የልጅና ባለቤታቸውን ጉሮሮ ለመድፈን እስከሚተጉ አባቶች ድረስ ዝቅ ተብሎ እግራቸው ታጥቦ፣ ጋቢ ተደርቦ እና ጉልበታቸው ተስሞ ተመስግነዋል ክብርና ምስጋና ቀርቦላቸዋል።
ግንቦት 15 እንደሌላው አለም ሁሉ ኢትዮጵያዊ መልክ የያዘ፣ ኢትዮጵያውያን አባቶች የሚመሰገኑበት፣ በኢትዮጵያ ካላንደር ኢትዮጵያዊ ምክንያት ኖሮት የሚከበር “የኢትዮጵያ አባቶች ቀን” ነው።


Source: FastMereja








No comments yet.