የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዛሬው ዕለት መቐለ፣ አክሱም፣ ሽሬ እና ሑመራን ጨምሮ ወደ ትግራይ ክልል ሊያደርጋቸው የነበሩ በረራዎችን መሰረዙን አዲስ ስታንዳርድ ያገኘው መረጃ አረጋገጠ።
በመቐለ የሚገኝ የአዲስ ስታንዳርድ ዘጋቢ እንደረጋገጠው የአውሮፕላን ማረፊያው ሰራተኞች ለዛሬ እረፍት እንዲወስዱ ተነግሯቸዋል።
ይሁን እንጂ በመቐለ የሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቲኬት ቢሮ ለዛሬ የታቀዱ በረራዎችን ሳይጨምር ሌሎች አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛል።
አንድ የቲኬት ቢሮ ሰራተኛ “ሲስተሙ እየሰራ ነው አገልግሎት እየሰጠን እንገኛለን ከነገ ጀምሮ ለሚደረጉ በረራዎች ቲኬት እየሸጥን ነው እንዲሁም የበረራ ቀጠሮዎችን እናሻሽላለን ሌሎች አገልግሎቶችንም እንሰጣለን ሲል ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጿል።
አክሎም “ነገር ግን በረራዎቹ ለምን ዛሬ እንደተሰረዙ ማናችንም አናውቅም” ብሏል።
ለዛሬ በረራ የያዙ መንገደኞች በረራው መሰረዙን የሚገልጽ የጽሁፍ መልዕክት ደርሷቸዋል። ለደንበኞች ከተላኩት መልዕክቶች አንዱ፤ “በጥር 21 ቀን 2018 ዓ.ም ከጠዋቱ 2:10 ከአዲስ አበባ ሊነሳ የነበረው በረራዎ ቁጥር ET0102 ባልታሰቡ ምክንያቶች ተሰርዟል። እባክዎን ለተጨማሪ መረጃ አየር መንገዱን ወይም የጉዞ ወኪልዎን ያነጋግሩ” ይላል።
የተሰረዘው በረራ ዛሬ ወደ ትግራይ ክልል አውሮፕላን ማረፊያዎች የሚደረጉ ሁሉንም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን የሚመለከት ሲሆን፤ መቐለን ብቻ ሳይሆን ሌሎች አውሮፕላን ማረፊያዎችንም ይጨምራል።
የአውሮፕላን ማረፊያው ሰራተኞች ነገ ወደ ስራ እንደሚመለሱ እና በረራዎች ስለመቀጠላቸው ተጠይቀው፣ የአየር መንገዱ ሰራተኞች ሁኔታው አሁንም ግልጽ እንዳልሆነ ገልጸዋል። አክለውም “ማወቅ የምንችለው ዛሬ ዘግይቶ ነው። ነገር ግን ሲስተሙ ነገ በረራ እንዳለ ያሳያል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዚህ ቀደም በትግራይ ጦርነት ወቅት ወደ ክልሉ የሚደረጉ በረራዎችን አቋርጦ ነበር።ሰኔ 2013 ዓ.ም የትግራይ ኃይሎች መቐለን ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ ወደ ክልሉ መዲና የሚደረጉ በረራዎች ለ18 ወራት ያህል ተቋርጠው ቆይተዋል። በረራዎቹ እንደገና የጀመሩት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ከሁለት ወራት በኋላ ነበር።
Source: Yeneta Tube









No comments yet.