#Ethiopia | አንድ የታሪክ ዋዜማ ላይ የምንገኝ ይመስላል፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያው”በብላቴናው” ፎቶ አሸብርቋል፡፡ ሙግትና ክርክሩ ካለፉት ወራት የምርጫ ቅስቀሳ በላይ አይሏል፡፡ በርግጥም ቴዎድሮስ ካሳሁን ልብ ያልተባለ Metropolitan ፖለቲከኛ መሆኑ አደባባይ ወጥቷል፡፡ የሚወዱት “ንግሥናን” ሰጥጠውታል፤ የሚጠሉት “ጥበብን ሸቀጥ” ማድረጉን ይለፍፉ ይዘዋል፡፡ ዳኝነቱን ላቆየውና ረጅሙን መንገድ በአጭር ልቃኘው፡፡
ቴዎድሮስ ካሳሁን በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ያለው ግዛት ሰፊ ነው፡፡ ቢሳካልን አንድ ቀን ዳጎስ ባለ መጽሐፍ እንመለስበት ይሆናል፡፡ ለዛሬ ግን ሁለት ነገሮችን ብቻ ልጠቀስ፡፡ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ አዲስ አበባ ተወልዶ ቢያድግም ለዘመናት ከቀየው የተሰደደ ነበር፡፡ ከጥላሁን እስከ ኤፍሬም ከብዙነሽ እስከ አስቴር አወቀ የተዘረጋው መንገድ ገራዶን ቢዘክርም፣አባ ሻዑልን ቢያስታውስም ለራሱ አድባር ግን ሥፍራ አልነበረውም፡፡ የአፈወርቅ ዮሐንስ ዘመን የይልማና አበበ ቀመር ጎጃምን ቢያስናፍቅም፣ ሐረርን ቢያስመኝም አርሲ ወስዶ ትግራይ ቢመልስም ስለ መዋያና ማደሪያው ግን ብዙ አልተጨነቀም፡፡
ይሁንና ቴዎድሮስ ካሳሁን በ1993 ዓ.ም አልበም ሲያወጣ አብዮት የታጠኑት የአራትና ስድስት ኪሎ ጎዳናዎች ቀና አሉ፡፡ አድዋ የዘመተው አራዳ ታቦቱና ንጉስ ያዘለው ፈረሱ ስገግ ብለው ታዩ፡፡ ሼኽ መንደፈርና ካዛንችስን ያኮረፈው ሙዚቃችን ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ፡፡ ልብ በሉ አዲስ አበባ ተራ ከተማ አይደለችም፡፡ ትእምርት ናት፡፡ ምስረታዋም ሆነ ዕድገቷ የወል ነው፡፡ የሁሉም ኢትዮጵያዊ፡፡ መውደቅ መነሳታችን፣ ለጉልበተኞች መገዛታችን፣ በደም የተሸመነ እጣ ፋንታችን ሁሉ ጎዳናዎቿ ላይ ተጽፏል፡፡
የቴዲ አረዳድ ግን ከዚህም ከፍ ይላል፡፡ የትውልድ መዲናውን ምልክት ያደርጋታል፡፡ የከተሜነት ምልክት፤ የጋራ እጣፋንታችን ተምሳሌት፡፡ ይህ ትርጉም ወደ ፖለቲካ ሲሄድ ሰፊ ነው፡፡ ያለፉትን አምሳ ዓመታት መንገድ ያስታውሳል፡፡ አብዮታችን የተጸነሰው እዚህ ሥፍራ ላይ ነው፡፡ ገበሬው ባላባቱ ላይ ተነሳ፡፡ ደርግ ተረገዘ የደደቢት ፈናን አራት ኪሎ ደረሰ፡፡ መንግሥቱ ኃይለማርያምም ሆነ መለስ ዜናዊ ለገጠር መወገናቸውን በአደባባይ ተናገሩ፡፡ የከተሜነት ፖለቲካ ከአራት ኪሎ ተባረረ፡፡ ላይመለስ የተሸነፈ መሰለ፡፡
ከዚያ በኋላ ያለው መንገድ ሥፍራ የመፈለግ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ኢትዮጵያን መናፈቅም ሊባል ይችላል፡፡ ፀጥታው ቢያስፈራም ኢዴፓ በ1992 ዓ.ም በፓርቲ ደራጃ የሚቻለውን ሞክሯል፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላም ቅንጅት በከተሜ ፖለቲካ ውስጥ ሌላ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡ ይህም ሆኖ የቴዲ አፍሮ ተጽዕኖ የላቀ ይመስለኛል፡፡ አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ ብሎ ከፊት ተሰለፈ፡፡
ቴዎድሮስ ካሳሁን ከአብዮቱ መለስ ያለው የኢትዮጵያ የብሄር ግንባታ ሒደት በወጉ አልወከለኝም የሚለው የሕብረተስብ ክፍል ሰንደቅ ነው፡፡ እርሱም ቢሆን ይህን መረዳቱ እርግጥ ይመስላል፡፡ ከአቡጊዳ እስከ ያስተሰርያል ድረስ ርዕዮተ-ዓለማዊ ልዩነቱን በሙዚቃዎቹ አንስቷል፡፡ ኢህአዴግ ሲያጣጥር “ጉራ ብቻ!!(ሰምበሬ) ሲል ተሳልቋል፡፡
በ2010 ዓ.ም ግን ተስፋን ሰንቆ ነበር፡፡ ቢያንስ እሱና እሱን የመሰለው የሕብረተሰብ ክፍል የኢትዮጵያ ፖለቲካ አካል እንደሚሆን፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ሲመጡ እንኳን ደስ አለን ማለቱ፣ ሚሊኒዬም አዳራሽ ተገኝቶ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና ፕ/ር ኢሳይያስ ፊት መናገሩ ሁሉ የምስክር ወረቀታችን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ብዙ አልተጓዘም፡፡ ከሦስት ዓመታት በኋላ ከሥርዓቱ ጋር ልዩነት እንዳለው በአደባባይ ያሳወቀ መሰለ፡፡
ትናንትም እንደ ጀንበር እያዩት ካይን ይርቃል
ኢትዮጵያ እንድትመጭ ስንት ቀን ይርቃል ፤ እያለ::
እዚህ ላይ ርዕዮ-ዓለማዊ ተቃርኖውን ለመረዳት ሩቅ መሔድ ሳይኖርብን ወቅታዊውን የመንግሥት አቋም ብቻ እናስታውስ፡፡ ዛሬ ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያ መቃብሩን ፈንቅላ ተንስታለች ብሎ ያምናል፡፡ ለትንሳኤ የተላለፈውን የመልካም ምኞት ቃል ልዋስና ኢትዮጵያ መግነዙን ፈትተዋለች፣መቃብሩን ፈንቅላዋለች ሲል ያወሳል::
ቴዎድሮስ ካሳሁን ግን በዚህ አያምንም፡፡ የሚንፍቃትን ኢትዮጵያ ገና እየጠበቀ ነው፡፡ ልዩነቱ የአልበርት ካሙን waiting for Godot የሚያስታውስ አልያም እንደ አይሁድ አምላክ ሰውን ሊያድን ተወልዷል አልተወለደም መከራከሪያ አይደለም፡፡ ፖለቲካነውና ያስፈራል፡፡
ቴዲ አፍሮ በ2013/14 ዓ.ም በአደባባይ ኢትዮጵያ አልመጣችም (እየመጣችም አይደለም) ካለ በኋላ በዛው አልጠፋም፡፡ ካለፈውም የጠነከረ ትችት አዝሎ ዳግም ከአንድ ዓመት በኋላ ተከሰተ፡፡ “ናዕት” በተሰኘ ሥራው ብዙዎች ሥርዓቱን ነው ባሉበት ስንኞቹ እንዲህ አለ፡፡
ቂምን ሻረውና ወይ ፍቅርን አንግሰው
ሁለት ሆኖ አያውቅም አንድ ነው አንድ ሰው
ቴዲ አፍሮ ለደጋፊዎች ግለሰብ አይደለም፡፡ ጊዜ የማያደበዝዘው ምልክት እንጂ ፤ያለመውድቅ ምልክት፣ የተስፋ ምልክት ፣ ያለመለወጥ ምልክት ፡፡ እርሱም ቢሆን ላይከዳቸው ለራሱ ቃል የገባ ይመስላል፡፡ ብዙ ሰው ልብ ብሎ መስማቱን ብጠራጠርም ቴዲ እንደ ሎሬት ጸጋዬ አዋሽ ግጥም፣ እንደ ባለቅኔው ደበበ ሰይፉ ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ መድብል ሁሉ ራሱ ለራሱ አዜሟል፡፡ በመግቢያ ስንኞቹ የሚደንቀኝን በማመንታቱ ልቤን የሚቧጭረውን “አልሔድ አልኝ” መውጫ ላድረግው፡፡
እዩት ይሄን ሰማይ ቀይ ኩታ መስሎ
ሊሸኝኝ ማለዳ ደህና ሁን ብሎ
ዛሬ ስል ነገ ስል ልቀይር ቦታ
የቆረጠው ልቤ ደግሞ አመነታ፡፡
ቀይ ኩታ የለበሰው ሰማይ የክፉ ዘመን ዋዜማ ነው ። ደግሞም የማለዳ ተፍጥሮ ክንብንብ፡፡ ቴዎድሮስ በዚህ ተስፋና ሥጋት ውስጥ ሆኖ ቦታ ልቀይር ይላል፡፡ ግን ልቡ እሽ አላላውም-ለስደት፡፡ ቁምነገሩ ግን እሱ ብቻ አይመስለኝም፡፡ ጥያቄው በቀይ ኩታ የተመሰለው ሰማይ መች ይጠራ ይሆን? የሚለው ነው፡፡
ጊዜ ለኩሉ! Maereg Getachew እንከተበው!!
Source: GetuTemesgen









No comments yet.