የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ከማሂ ኢቨንትስ (Mahi Events) ጋር በመተባበር “Miss African Essence International Pageant 2026″ የተሰኘ ዓለም አቀፍ የቁንጅና ውድድር በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ አስታወቀ።
የአፍሪካውያን ሴቶችን አቅም፣ ባህልና ውበት ለማስተዋወቅ ያለመው ይህ ውድድር የፊታችን ሚያዝያ 24 ቀን 2018 ዓ.ም ከምሽቱ 11 ሰዓት ጀምሮ በወዳጅነት ፓርክ እንደሚካሄድ የተገለፀ ሲሆን ውድድሩ በዋናነት አዲስ አበባን ለታላላቅ ዓለም አቀፍ ሁነቶች ዝግጁና ተመራጭ መዳረሻ አድርጎ ለማስተዋወቅ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው በመግለጫው ተመላክቷል።
ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉበት ይህ መርሐ ግብር፣ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ ሲሆን፤ ተሳታፊዎቹ ለ15 ቀናት የአመራርነት ስልጠና እና የባህል ልውውጥ የሚያደርጉበት ቆይታ እንደሚኖራቸዉ ተነግሯል።
የዝግጅቱ መሥራችና የማሂ ኢቨንትስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ማህሌት ገብረዮሀንስ እንደገለጹት፣ መርሐ ግብሩ ከመድረክ ትርኢት ባለፈ የባህል ዲፕሎማሲ መድረክ ሆኖ እንደሚያገለግል ገልፀዋል።
ወ/ሪት ማህሌት አክለዉም ተወዳዳሪዎቹ በኢትዮጵያ የተለያዩ የቱሪስት መስህቦች አካባቢ በሚቀርጿቸው ምስሎች አማካኝነት የሀገርን ገጽታ የመገንባት፣ የአፍሪካን ወግና ታሪክ ለዓለም የማሳየት እንዲሁም ሴቶች በአመራርነትና በሥራ ፈጣሪነት ዘርፍ እንዲበቁ የማስቻል ዓላማ እንዳለዉ ገልፀዋል።
የውድድሩ አሸናፊ የሁለት ሚሊዮን ብር የገንዘብ ሽልማት የምታገኝ ሲሆን፣ በተጨማሪም እስከ ካናዳ ድረስ በመጓዝ ኢትዮጵያንና አፍሪካን የማስተዋወቅ ዓለም አቀፍ የአምባሳደርነት ዕድል እንደምትቀዳጅ ተገልጿል።
ዝግጅቱ በኢኮኖሚ ረገድ ለሀገር ውስጥ ባለሙያዎች፣ ለዲዛይነሮችና ለፈጠራ ኢንዱስትሪው ሰፊ የገበያ ትስስርና የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር በመግለጫው የተጠቀሰ ሲሆን “አንድ ሴትን ማብቃት ሀገርን ማብቃት ነው” በሚል መሪ ቃል የሚከናወነው ይህ ውድድር፣ ኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፏን ከውበትና ከባህል ጋር አቀናጅታ የምታሳይበት ስትራቴጂያዊ መድረክ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ሚያዝያ 24 ቀን በሚካሄደው የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ በርካታ እንግዶችና የዘርፉ ባለሙያዎች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል። ለበለጠ መረጃ ከታች ባለው ሊንክ ይጠቀሙ
Instagram page from Mahi events
https://www.instagram.com/mahievents_et?igsh=MWdob3NneXNscWl0aw%3D%3D&utm_source=qr
@Mahievents_et



Source: Yeneta Tube









No comments yet.