📢 ኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ ወደሥራ መግባቱን አበሰረ፣
__
ኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ ከኢፌድሪ የጤና ሚኒስቴር ጋር ለ175 + 20 የልብ ህሙማን ህጻናት ነጻ የልብ ቀዶ ህክምና ለመስጠት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ በመፈረም ወደሥራ መግባቱን አበሰረ።
የመግባቢያ ሰነዱ በጤና ሚኒስቴር እና የልብ ቀዶ ህክምና አጋር በሆኑ የግል እና የመንግስት ሆስፒታሎች የተፈረመ ሲሆን፤ ነጻ የልብ ቀዶ ህክምና ዘመቻው ከሚያዝያ 12 ጀምሮ ለ45 ቀናት በግል እና በመንግስት ሆስፒታሎች የሚሰጥ ይሆናል።
የመግባቢያ ሰነዱን ከጤና ሚኒስቴር ጋር የተፈራረሙት
የኸርት ቱ ኸርት ችልድረን ኤይድ፣ የኢትዮጵያ የልብ ማህበር፣ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እና ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ፣ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ የቅዱስ ዼጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ የኢትዮ-ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል፣ የኤልውዘር የልብ ህክምና ማዕከል እና የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን መርጃ ናቸው።
የልብ ቀዶ ህክምና ዘመቻው በዘርፉ ያለውን ጫና ለማቃለል የጎላ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የተናገሩት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፤ የመንግስት እና የግል ተቋማት በትብብር ሲሰሩ ዘለቄታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ ገልፀው፣ የመግባቢያ ሰነዱን የፈረሙ አካላትን አመስግነዋል፡፡
በዚሁ ስምምነት መሰረት :-
❤ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 50፣
❤ የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን መርጃ ማእከል 50፣
❤ ኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል በአዲስአበባ ከተማ 50፣ በጅግጅጋ ከተማ 20 ፣
❤ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እና ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ እንዲሁም የቅዱስ ዼጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 25 ፣
❤ የኤልውዘር የልብ ህክምና ማዕከል 5 ፤ የልብ ሕሙማን ሕፃናትን ተቀብለው ተገቢውን ሕክምና ይሰጣሉ።
በዚሁ ስምምነት መሰረት ከኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል በዶ/ር ሺብቆም ታምራት የሚመራ 15 አባላት ያሉት የሕክምና ቡድን በዛሬው ዕለት ወደጅግጅጋ የተጓዘ ሲሆን ከነገ ሚያዚያ 9/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለ20 የልብ ሕሙማን ሕክምና መስጠት እንደሚጀምር ኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ ገልጿል።
ከጣልያን ሀገር የሚመጡ የሕክምና ባለሙያዎች ቡድን ሚያዚያ 16/2018 ዓ.ም የኢትዮጵያውያንን የሕክምና ቡድን ይቀላቀላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል።
የታካሚዎች መረጣ በተመለከተ ከኢትዮጵያ ልብ ማኀበር ጋር በመተባበር ያለምንም አድልኦ ወረፋ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ታካሚዎች እንደቅደምተከተላቸው በጥንቃቄ የሚመረጡ መሆኑም ተረጋግጧል።
“በኢትዮጵያውያን ሐኪሞች ለኢትዮጵያውያን ሕጻናት ልብ ጤና” በሚል መሪ ቃል ለሚከናወነው ለዚህ መርሐግብር ላይ ለሚሳተፉ የመንግስትና የግል ሆስፒታሎች ፤ ኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ በቅርቡ በዋሽንግተን ዲሲ ካሰባሰበው ገቢ በመጠቀም
አስፈላጊውን የመድሃኒትና የሕክምና ግብዐቶች እንደሚያቀርብ ለማወቅ ተችሏል።
በመጨረሻም አቶ ብርሃን ተድላ የኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጻሚ እና የኸርት ቱ ኸርት ፋውንዴሽን መስራችና የቦርድ ሰብሳቢ ለዛሬው ታላቅ የስምምነት መርሐግብር መሳካት አስተዋፅኦ ያደረጉ የጤና ሚኒስቴር እና የሆስፒታሎች ከፍተኛ አመራሮች እና በሥራው ለሚሳተፉ የሕክምና ባለሙያዎች ከፍተኛ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። አያይዘውም በቅርቡ በአሜሪካን ሀገር በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ የተካሄደው የገቢ ማሰባሰብ እንዲሳካ በገንዘብና በቴክኒክ የደገፉ፣ ገንዘባቸውን ለዚህ በጎ ተግባር የከፈሉ ወገኖች የላቀ ምስጋና በማቅረብ፤ ቃል ገብተው ያልከፈሉ ወገኖች እንዲከፍሉ ጥሪ አቅርበዋል።



Source: FastMereja









No comments yet.