#FastMereja I ኢዩደን ሚዲያ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (INSA) ዕውቅና ያገኘ እና በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው “Cultural Ambassador Award” የባለተሰጥኦዎች የዲጂታል መወዳደሪያ ድረ-ገጽን በስካይላይት ሆቴል በይፋ አስመረቀ።
በመረቀው መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢዩደን ሚዲያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል ጥሩነህ፣ መድረኩ የኢትዮጵያን ባህል ለዓለም ለማስተዋወቅና በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኙ ባለተሰጥኦዎችን በአንድ የዲጂታል መንደር ለማገናኘት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል። ውድድሩ በዘመናዊ የዲጂታል መሠረተ ልማት የታገዘና የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ሰርተፊኬት የተሰጠው መሆኑም ተገልጿል።
ይህ ግዙፍ ውድድር በስድስት ዘርፎች ማለትም በድምፃዊነት፣ በባህላዊ ውዝዋዜ፣ በባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ፣ በሥነ-ጽሁፍና ግጥም፣ በምርቶችና ፋሽን ዲዛይን እንዲሁም በባህላዊ ትወና ዘርፎች የሚካሄድ ነው። ተወዳዳሪዎች ከዛሬ ሚያዝያ 6 ጀምሮ እስከ መስከረም 1 ቀን 2019 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በድረ-ገጽ (CulturalAmbassadorAward.com) ወይም በቴሌግራም እና ዋትስአፕ ቁጥሮች +251953540101 ወይም +251953540102 በመጠቀም መመዝገብ ይችላሉ።
በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ተወዳዳሪዎች የባህል ልብስ መልበስ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ ይዘቶቹም ከፖለቲካ የጸዱና የብሔር ማንነትን የማይነኩ መሆን እንዳለባቸው የውድድሩ ደንብ ያስገድዳል። የኢትዮጵያ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ማስተር ካርድ ከኢዩደን ሚዲያ ጋር በመተባበር ለውድድሩ ስኬት የሚሰሩ ሲሆን፣ አሸናፊዎችን የመለየት ሥልጣን ሙሉ በሙሉ ለሕዝብ ድምፅ ተሰጥቷል። አሸናፊዎችም ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት እንደሚጠብቃቸው ተገልጿል።



Source: FastMereja









No comments yet.