ሰሞንኛ
(በእውቀቱ ስዩም)
የኢትዮጵያ ስልጣኔ መስራች የሆኑት የአክሱም ነገስታት በንግስና ቀናቸው በዋናነት ሶስት ስርአቶችን ይፈፅሙ ነበር፤ መጀመርያ እጩው ንጉስ አንበሳ ይገድላል፤ ከዚያ ታጅቦ ወደ ደጀሰላም ሲመጣ የጽዮን ልጆች የተባሉ ደናግላን፣ ንጉሱን እየዘፈኑ ይቀበሉታል ፤ ወርቅ አፍሶ ይበትንላቸዋል፤ ከዚያ በሁዋላ ነው በጳጳሱ አማካኝነት የሚቀባው፤
አንበሳውን ግድያ የንጉሱን ጀግንነትና ጠንካራነት ምልክት ነው፤ አገር የመጠበቅ አቅም አለው ብሎ ህዝቡ አንዲተማመንበት ያደርጋል፤ የዘፋኞቹ አቀባበልና የወርቅ ስጦታው ደግሞ ፣ንጉሱ ለኪነጥበብ ያለው ስሱነት ( Artistic sensibility ) ማሳያ ነው፤
ያገር ዳር ድንበር ሲደፈር ከወታደር ጋር አዝማሪም ይዘምታል ፤ አዝማሪ ሳያስከትል የዘመተ ንጉስ ኖሮን አያውቅም፤ የጀግኖች ወኔ አዋላጅ ነው አዝማሪ፤ ፈሪ ይወቅሳል፤ ጠላትን ይዘልፋል፤ ከዚያ ባለፈ የጋዜጠኝነትንና የታሪክ መዝጋቢነትን ሚና ይጫወታል
ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ
ያለው አዝማሪ የጦርሜዳ ዜና ዘጋቢ ነው፤ ዘገባው እኛ ጋ ሲደርስ ታሪክ ሆኑዋል፤
በጦርሜዳ ላይ ለሀገራቸው ህይወታቸውን የገበሩ አዝማሪዎች ጥቂት አይደሉም፤ በኛ ትውልድ እንኩዋ በሻእብያ ጥይት ሜዳ የቀረችው ንግስት አበበ አንዴት ትዘነጋለች፤ የጥላሁን ገሰሰ እንባና ዜማ የንግስት አበበ ደም ባቆየው አገር ውስጥ ነው ውር ውር የምንለው፤ በየጊዜው ፣ ፍርድ እንዲቃና ግፍ አንዲወገድ ፣ ሰላም አንዲሰፍን የሚጎተጉቱም አዝማሪዎች ናቸው፤
ሌላው ይቅርና የምንበላው የጤፍ አንጀራ በዘፈን ተገፍቶ ሞሰባች ላይ አንደደረሰ ዘንግተናል፤ ገበሬ እያንጎራጎረ አርሶ እየዘፈነ ይወቃል፤ የዘፈንን ያክል ድካም አቅላይ አይገኝማ!
ኢትዮጵያ ውስጥ በየጊዜው በየመድረኩ ዘው እያሉ፣ ዘፈንና ዘፋኝን የሚኮንኑ፣ በዘፈን የሚደሰቱ ሰዎች ላይ ፍርሀትና ፀፀትን የሚነዙ የእግዜር ወኪል ነን ባዮች ሞልተዋል፤ አንዱ ባለፈው በቴዲ ዘፈን መለቀቅ ዋዜማ ላይ ዘፈኑ አንዳይከናወንለት ሲራገም የነበረ ነው፤ በርግማኑ ማግስት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ተመልካች ዘፈኑ ላይ ተመሰጠበት፤ ይህ ክስተት፣ እግዜር ከሙዋርተኛ ይልቅ ዘፋኝን እንደሚረዳ ትልቅ ማሳያ ይመስለኛል፤
ይሄ ሰውየ በቀደም አርባምንጭ ድረስ ሄዶ፣ ከሞተ አዞ አጠገብ ፎቶ በመነሳት ዘንዶውን ወጋሁት እያለ ሲፎክር ነበር፤ አንድ ሰው ፣ በዚህ ዘመን በምግብ እጥረትና በርጅና የሞተ አዞ ሬሳ ላይ ሲፎክር እንደማየት የሚያስገርም ነገር የለም! በሌላ ጊዜ ይህ ዠለስ፣ ማይክል ጃክሰን በሰይጣን መንፈስ የሚመራ ዘፋኝ ነበር ሲል ሰማሁት፤ ማይክል ጃክሰን ባንድ ነጠላ ዜማ ብዙ ሚሊዪን ዶላር አዋጥቶ የተራበ ህዝባችንን የረዳ እጅግ ደግ ሰው መሆኑን የሚያውቅ አይመስለኝም ፤ ወይም ሳያውቀው ለሰይጣን የገፅታ ግንባታ እየሰራ ነው!
Source: Yeneta Tube









No comments yet.