በኢትዮጵያ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮች መድረክ የሆነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ እስካሁን ዕውቅና የሰጣቸው ብሔር ብሔረሰቦች ቁጥር 76 ብቻ መሆኑን ገለጸ።
የምክር ቤቱ አባል አቶ ክብሩ ማሞ፣ በሀገሪቱ የሚገኙ የብሔር ብሔረሰቦች ቁጥር በተለያየ አሃዝ ሲገለጽ እንደቆየ አስታውሰዋል።
ይህ ቢሆንም ምክር ቤቱ ጉዳዩን የሚከታተልና መረጃዎችን የሚያጠና ቡድን በማዋቀር ባከናወነው ጥናት 76 ብሔረሰቦች ዕውቅና እንዳገኙ አረጋግጠዋል።
ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የማንነት ዕውቅና ይሰጠን ጥያቄ በተደጋጋሚ እንደሚቀርብ የጠቀሱት አቶ ክብሩ፣ በአሁኑ ወቅት የሚነሱ ጥያቄዎች ዋነኛ ምክንያት ፖለቲካዊ ፍላጎቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።
ቀደም ሲል የአንድ ብሔር አባል የነበሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች አለመስማማት ሲፈጠር ወይም የፖለቲካ ኃይል ማግኘት ሲፈልጉ፣ በጎሳ ተደራጅተው ራሳቸውን እንደ ብሔር በመቁጠር ጥያቄ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል። ምክር ቤቱ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች ሲቀርቡለት በጥንቃቄ እንደሚመረምር ተገልጿል።
ጥያቄ አቅራቢው ማኅበረሰብ የራሱ የሆነ ማንነት፣ መልክአ ምድርና ባሕል ያለው መሆኑ ከተጠና በኋላ ውሳኔ እንደሚሰጥም አቶ ክብሩ አብራርተዋል። ለዚህም እንደ ምሳሌ የስልጤ ዞንን ጥያቄ እና የተሰጠውን ምላሽ ጠቅሰዋል።
ጉዳዩን የፖለቲካ ኃይል ማግኛ የማድረግ ዝንባሌዎች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ክብሩ መሰል ጥያቄዎች ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ምላሽ እንደሚያገኙ አመልክተዋል።
ምክር ቤቱ ከዕውቅና በተጨማሪ የማንነት ጉዳዮችን የመመልከት፣ ሕገ-መንግሥቱን የመተርጎም፣ የገቢ ክፍፍል ቀመር የመወሰንና በጀት የመመደብ ሕገ-መንግሥታዊ ሥልጣን እንዳለውም ተጠቅሷል።
በ ሙሉጌታ በላይ
Source: Yeneta Tube









No comments yet.