#FastMereja I የፌስቡክ እና የኢንስታግራም እናት ኩባንያ የሆነው ሜታ፣ ለሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ፕሮጀክቶች የሚያወጣውን ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ ለመጨመር በማቀዱ የጠቅላላ ሰራተኞቹን 10 በመቶ ወይም 8,000 ያህል ሰራተኞችን በሚቀጥለው ወር ከስራ እንደሚያሰናብት አስታወቀ። ኩባንያው ከዚህ በተጨማሪ ቀደም ሲል ክፍት የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የሥራ መደቦችን እንደማይሞላ ለሠራተኞቹ ባስተላለፈው የውስጥ ማስታወሻ ገልጿል።
የሜታ ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርክ ዙከርበርግ በዘንድሮው ዓመት ብቻ ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ልማት 135 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ለማድረግ ማቀዳቸውን ተከትሎ ይህ የሠራተኛ ቅነሳ መወሰኑ ተገልጿል። ይህ የወጪ መጠን ኩባንያው ባለፉት ሶስት ዓመታት በድምሩ ለዘርፉ ካወጣው ገንዘብ ጋር እኩል ነው። ዙከርበርግ የ”AI” መሣሪያዎችን የሚጠቀሙ ሠራተኞች ምርታማነት መጨመሩን በመጥቀስ፣ ቀደም ሲል ትልቅ ቡድን የሚጠይቁ ሥራዎችን አሁን በአንድ ሰው ማከናወን እንደሚቻል በጥር ወር ላይ መናገራቸው ይታወሳል።
ከሥራ ቅነሳው ጎን ለጎን ሜታ የ”AI” ሞዴሎችን ለማሰልጠን የሠራተኞቹን የኮምፒውተር እንቅስቃሴ መከታተል መጀመሩ በሠራተኞች ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል። ኩባንያው እ.ኤ.አ. ከ2022 ጀምሮ በተለያዩ ዙሮች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን የቀነሰ ቢሆንም፣ የዘንድሮው እርምጃ ከ2023 ወዲህ የተመዘገበ ትልቁ የሥራ ስንብት ይሆናል።
ይህ በቴክኖሎጂው ዘርፍ የታየው የሠራተኛ ቅነሳ ማዕበል ሜታን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ታላላቅ ኩባንያዎችንም አጠቃሏል። አማዞን 30,000፣ ኦራክል 10,000 እንዲሁም ማይክሮሶፍት በሺዎች ለሚቆጠሩ ነባር ሠራተኞቹ በፈቃደኝነት የሥራ ስንብት ክፍያ እያቀረበ ይገኛል። አብዛኞቹ ኩባንያዎች ለውሳኔያቸው እንደ ምክንያት የጠቀሱት የሰው ሰራሽ አስተውሎት አቅም እያደገ መምጣቱንና ለዘርፉ የሚመደበው መዋዕለ ንዋይ መጨመሩን ነው።
Source: FastMereja









No comments yet.