#FastMereja I በኢትዮጵያ ሚዲያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ የግል የቴሌቪዥን ጣቢያ የዓለም ዋንጫን በነፃ በቀጥታ የማስተላለፍ ታሪካዊ መብት ማግኘቱ ተበሰረ። ሀገሬ ቴሌቪዥን (Hagerie TV) በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በጋራ የሚዘጋጀውን የ2026 የፊፋ ዓለም ዋንጫ ለኢትዮጵያውያን ተመልካቾች በነፃ እንደሚያስተላልፍ በይፋ አስታውቋል።
ጣቢያው ይህንን መብት ያገኘው ከዓለም አቀፉ የሚዲያ ተቋም “ኒው ወርልድ ቲቪ” ጋር ስምምነት ላይ በመድረስ ነው። በዚህም መሠረት ከሰኔ 04 እስከ ሐምሌ 12/2018 ዓ.ም (እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር) በሦስቱ ሰሜን አሜሪካ ሀገራት የሚካሄዱትን ተጠባቂ ጨዋታዎች በቀጥታ ወደ ቤታችን ያመጣል።
ሀገሬ ቴሌቪዥን በቀጥታ ከሚያስተላልፋቸው ጨዋታዎች በተጨማሪ፣ በሰዓት ልዩነት ምክንያት በቀጥታ ለማሳየት የማይመቹ ግጥሚያዎችን በድጋሚ (Highlight) ለተመልካቾች እንደሚያቀርብ ገልጿል። ጣቢያው ለውድድሩ ልዩ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የጠቀሰ ሲሆን፣ በተለይም የአፍሪካ ሀገራትን ተሳትፎ መሠረት ያደረጉ ትንታኔዎች፣ ፈጣን መረጃዎች እና ጥልቅ ስፖርታዊ ዘገባዎችን ለማቅረብ ሪፖርተሮቹን ማዘጋጀቱን አስታውቋል።
ከዓለም ዋንጫው በተጨማሪ ጣቢያው ሌላ የምሥራች ይዟል። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸውን የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ውድድሮች እስከ 2029 ዓ.ም ድረስ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት በብቸኝነት የማስተላለፍ መብት ማግኘቱንም በሰጠው መግለጫ አረጋግጧል። ይህ እርምጃ የግል ሚዲያው በስፖርቱ ዘርፍ ያለውን ተደራሽነት ከፍ የሚያደርገውና ለንግድ ተቋማትም ትልቅ የማስታወቂያ ዕድል የሚፈጥር መሆኑ ተመልክቷል።
Source: FastMereja









No comments yet.